የኢትዮጵያ የባህር ኃይል መልሶ መቋቋሙ የሀገርን ክብር ከፍ የሚያደርግ ነው-የቀድሞ የባህር ኃይል አባላት - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የባህር ኃይል መልሶ መቋቋሙ የሀገርን ክብር ከፍ የሚያደርግ ነው-የቀድሞ የባህር ኃይል አባላት
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ የባህር ኃይል መልሶ መቋቋሙ የሀገርን ክብር ዳግም ከፍ የሚያደርግ ነው ሲሉ የቀድሞ የባህር ኃይል አባላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ታሪክ የሚጀምረው ከሺህዎች ዓመታት በፊት ቢሆንም በዘመናዊ መልኩ የተቋቋመው ግን በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1948 ዓ.ም ነው።
በደርግ ዘመንም የባህር ኃይሉ የበለጠ አደረጃጀቱ ሰፍቶ፣ በጠንካራ ወታደራዊ መርከቦችና ትጥቆች ተደራጅቶ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ኃይል ነበር።
ኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ ወጪና ንግድ መመላለሻ በሆነው በጅቡቲ ኮሪደር የባህር ኃይል በ2011 ዓ.ም መልሳ ማቋቋሙ ይታወሳል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የቀድሞ ባህር ኃይል ረዳት የትምህርት መኮንን ሌፍተናንት ዮሴፍ ሸጋው፥ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የተቋቋመው ያለንበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እና የቀይ ባህር አካባቢ ከፍተኛ ጂኦ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ስላለውና የብዙዎች ፍላጎት ያረፈበት በመሆኑ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ነው ብለዋል።
የባህር ኃይሉ መቋቋም የህልውና ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው፤መርከቦችን ለመጠበቅ፣ የቀጣናው ደህንነትን ለማረጋገጥና ከየትኛውም አካባቢ የሚሰነዘርን ጥቃት ለመመከት አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት።
የቀድሞው ባህር ኃይል በወቅቱ የኢትዮጵያን ከ1000 ኪሎ ሜትር በላይ የባህር ወሰን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚቆጣጠር እንደነበርም አንስተዋል።
ለ35 ዓመታት የተገነባው የቀድሞው የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በውቅያኖሶች አስተማማኝ ደጀን እንደነበር ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው በኩል አንድም ጊዜ ተደፍራ የማታውቀውም በባህር ኃይሏ ጥንካሬ መሆኑን አንስተዋል።
ሌላኛው የቀድሞ የባህር ኃይል አባል ሊዲንግ ሲማን ዳምጠው ጉግሳ፤ የባህር ኃይሉ በትጥቅ፣ በሰው ኃይል፣ በዘመናዊ መርከበኞች የተደራጀ እንደነበር አስታውሰዋል።
የባህር ኃይሉ በተለያዩ ሀገራት በሰለጠኑ አባላትና አመራሮች የሚመራና ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከሌሎች ትላልቅ የባሀር ኃይል አባላት ጋር ትልቅ ግንኙነት የነበረው መሆኑን አንስተዋል።
በቀድሞው የባህር ኃይል ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት ፔቲ ኦፊሰር ወንደሰን አሰፋ፤ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ሀገራችን ታፍራና ተከብራ እንድትኖር በማድረግ በአፍሪካ ግዙፍ ስም ነበረው ብለዋል።
በሰፊ ሀብትና በረጅም ዓመታት የተገነባው ተቋም በአንድ ሌሊት በፖለቲካዊ ውሳኔ መፍረሱ በታሪክ ጥቁር ነጥብ መሆኑን ገልጸው ሀገርም በውሳኔው ዋጋ ከፍላለች ነው ያሉት።
ነገር ግን መንግሥት ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ መከላከያ ሠራዊቱን በምድር ጦር፣ በአየር ኃይል፣ በባህር ኃይል፣ በህዋና በሳይበር አውዶች በጠንካራ ሁኔታ እያደራጀ መሆኑ ሀገርን የሚያኮራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ካለው አለመረጋጋትና የኃያላን ሽኩቻ አንጻር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የባህር ኃይሉ ዳግም እንዲቋቋም መወሰኑና ወደ ተግባር መገባቱም አስደናቂ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገራችን የባህር በር ባይኖራትም ሌሎች ሀገራት እንደሚያደርጉት ሁሉ በዲፕሎማሲያዊ ትብብር የባህር ኃይል የጦር ምድብ ማቋቋም እንደምትችል ጠቁመዋል።
ከብዙ ርቀት መጥተው በራችን ላይ የጦር ሰፈር ማቋቋማቸው እንደ ሀገር የሚያስቆጭ መሆኑን አንስተው፥ ኢትዮጵያም ብሔራዊና አካባቢያዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የባህር ኃይሏን ማጠናከር የግድ ይላታል ነው ያሉት።
"የባህር ኃይሉ ዳግም መቋቋም የእናታችን ቤት ፈርሶ እንደገና ሲገነባም እንደማየት ነው" ያሉት የቀድሞ የባህር ሃይል አባላት፤ የባህር ኃይል ትንሳኤ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዳግም ስሟን ከፍ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
አሁን መሰረታዊ ባህረኞችን የማሰልጠንና መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ጅምር መኖሩ የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው፤ የቀድሞ የባህር ሃይል አባላትም ለሚወዷት ሀገራቸው አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃ እንድትኖር ጀግንነትን፣ ቴክኖሎጂን እና ታሪካዊ እሴትን ለወጣቶች ለማውረስም እንደ አዲስ እየተቋቋመ ካለው የባህር ሃይል ጋር በመስራት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የባህር ኃይል በቅርቡ በናቪጌሽን፣ ፣ ኤሌክትሪሲቲ፣ በኮሙኔኬሽን፣በአርማመንትና በሌሎች መሰል ሙያዎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሰለጠኑ ባህረኞችን ማስመረቁ ይታወሳል።