የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሃገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማዘጋጀት ስራ መጀመሩን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሃገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማዘጋጀት ስራ መጀመሩን አስታወቀ
አሶሳ ፤ ሰኔ 23 ቀን 2015 (ኢዜአ) :- የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በምክክሩ የሚሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማዘጋጀትና አጀንዳ ለማሰባሳብ ስራ መጀመሩን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ዛሬ በአሶሳ ከተማ በሰጡት መግለጫ ፤ኮሚሽኑ ከክልሉ በሃገራዊ ምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎች እና አጃንዳ ለመለየት ስራውን በይፋ ጀምሯል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሚገኙ 22 ወረዳዎች እና አምስት የከተማ አስተዳደሮች ከ12 ሺህ 150 በላይ ሰዎች በሃገራዊ ምክክሩ እንደሚሳተፉ የሚጠበቅ መሆኑን አስረድተዋል።
ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ከክልሉ ለተውጣጡ ተባባሪ አካላት ስልጠና መስጠት እንደሚጀመር ገልጸዋል።
በስልጠናው የሚሳተፉት እነዚህ ተባባሪ አካላት ዳኞች፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሃገር ሽማግሌዎች እና መምህራን መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ሰልጣኞቹ ወደየ ወረዳቸው ተመልሰው በሃገራዊ ውይይቱ የሚሳተፉትን የክልሉን ነዋሪዎች እንደሚያዘጋጁ አመልክተዋል።
የክልሉ ህዝብ በሃገራዊ ምክክሩ በሚገባ እንዲሳተፍ በተለይም ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በበቂ ሁኔታ እንዲወከሉ የሚደረግ መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን ገልጸዋል።