የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ተከታታይ አጀንዳዎችን ቀርጾ እየሰራ ነው-አቶ ሰይፈ ደርቤ

አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ብሔራዊ መግባባትን የሚፈጥሩ ተከታታይ አጀንዳዎችን ቀርጾ እየሰራ እንደሚገኝ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ገለጹ።

አገራዊ እሴቶች ለብሔራዊ መግባባት እና ለአገር ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ የሚዳስስ የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ አባል ወይዘሮ ሚሊዮን ተረፈ፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች እና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ “ኢትዮጵያ ብዝሃነትን የተላበሰች፣ ልየ ልዩ ማንነት ያላቸው ሕዝቦች የሚኖሩባት እና ሕብረ ብሔራዊ መገለጫዋ የሆነች አገር ናት” ብለዋል።

እንደ ሕዝቡ ብዛት እና ስብጥር የተለያዩ ምልከታዎች እና አተያዮች መኖሩ ተፈጥሯዊ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዋናው ጉዳይ እይታው እና የሃሳብ ብዝሃነቱ ሰላምን የማይጎዳ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የማይጻረር፣ መግባባት እና መተማመን እንዲሁም የሚያጋጥሙ ግጭቶችን የሚተዳደሩበት ሁኔታ ላይ የጋራ አረዳድ መፍጠሩ መሆኑን አንስተዋል።

የሰላም ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሰላም ጉዳዮች ጋር ተያያዥ ስራዎችን የሚያከናውኑ ተቋማት ብሔራዊ መግባባት ላይ የሚያከናውኗቸውን ስራዎች የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እና ሌሎች መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ የማድረስ እና የማስገንዘብ ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ኢዜአ ብሔራዊ መግባባት ላይ ያተኮሩ ተከታታይ አጀንዳዎችን በመቅረፅ እየሰራ እንደሚገኝ እና ይህም ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የሚያሻግሩ እና አንድነት የሚያስጠብቁ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ነው አቶ ሰይፈ ያስረዱት።

ሁሉም ጉዳይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ጥላ ስር እንዲሆን ኢዜአ ተልኮው በሆነው የብሔራዊ መግባባት የመፍጠር ጉዳይ የበኩሉን የመወጣት ስራ ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ለዘላቂ ሰላም መስፈን እየሰራ የሚገኘው የሰላም ሚኒስቴር የውይይት መድረኩ እንዲዘጋጅ በማድረግ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለውይይቱ መካሄድ ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም