ቀጥታ፡

በአፍሪካ ከአየር ብክለት ነፃ የአውሮፕላን ነዳጅ ማምረት የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት አለ- ዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር

አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015(ኢዜአ)፦በአፍሪካ ከአየር ብክለት ነፃ የአውሮፕላን ነዳጅ ማምረት የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት መኖሩን የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር /አያታ/ ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋሊሽ  ገለጹ።

ከተለያዩ ተረፈ ምርቶች የሚመረተውና ከአየር ብክለት ነፃ የሆነው የአውሮፕላን ነዳጅ "ሰስቴነብል አቪዬሽን ፊዩል" /ሳፍ/ በመባል ይታወቃል።

በኢትዮጵያም ይህንኑ ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ ለማምረት የሚያስችል እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶችና ከቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑ ተነግሯል። 

የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ማህበር /አያታ/ ዋና ዳይሬክተር ዊሊ ዋሊሽ፤ በዓለም በሁሉም አየር መንገዶች እ.አ.አ በ2050 ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን ካርበን ዜሮ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

ለዚሀም ስኬት ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ በስፋት ማምረት የሚያስችል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት መኖሩን ጠቁመዋል።


 

አገራት እቅዱን ለማሳካት የሚያስችል እንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው በተለይም የአፍሪካ አገራት ለምርቱ ምቹ ሁኔታና በቂ ሃብት አላቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድም ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ ነዳጅ ለማምረት የተጀመረው እንቅስቃሴ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገራት ምርቱን ሲጀምሩ የአየር ብክለትን ከመከላከል ባለፈ ሰፊ የስራ እድል በመፍጠርና የኢኮኖሚ ጠቀሜታን ከማሳደግ አንፃር ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ እ.አ.አ በ2050 በዓለም አቀፍ የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማኅበር ሁሉም አየር መንገዶች ወደ አየር የሚለቀቀውን ካርበን ዜሮ ለማድረግ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ላይ መሆኑ ይታወቃል።

ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ የአውሮፕላን ነዳጅ ከመኖ ተረፈ ምርት የሚዘጋጅ ሲሆን በህይወት ዑደት ተፈጥሮን በማዛባት የሚደርሰውን የካርበን ልቀት የሚያስቀር ይሆናል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም