በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገራዊ ጥቅም፣ የጋራ ማንነትና የጋራ ዕሴቶች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ይገባል--የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገራዊ ጥቅም፣ የጋራ ማንነትና የጋራ ዕሴቶች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ይገባል--የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈንና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት በሀገራዊ ጥቅም፣ የጋራ ማንነትና የጋራ ዕሴቶች ላይ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፓናል ውይይት "አገራዊ ዕሴቶች ለብሔራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የተለያዩ የፖለቲካ፣ የቋንቋ፣ የሀይማኖት እና አስተሳሰቦች ያሉባት የብዝሃነት ሀገር ናት።
ልዩነቶች የአብሮነታችን ህብረ ቀለሞች ቢሆኑም በረጅም የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ግንባታ ጉዞ ብሔራዊ እሴቶችን የሚሸረሽሩ የህግ የበላይነት የሚፃረሩ፣ ከኢትዮጵያዊነት እሴት ያፈነገጡ ግብረ-ገብነት የጎደላቸው የሀገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ችግሮች ይስተዋላሉ።
የሀገር ግንባታ ሂደት እንጂ በአንዴ የሚጠናቀቅ ባለመሆኑ እነዚህን ችግሮች ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እንቅፋት መሆናቸው አይቀርም ብለዋል።
በመሆኑም ሂደት የሆነውን የሀገረ መንግስት ግንባታ እውን ለማድረግ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚሰናሰል ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን የፈጠሩ ሀገራት ለዘላቂ ሰላም ቅርብ መሆናቸውን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያንም የገነባነውን እሴት ጠብቀን የሀገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት መፍጠር ይገባናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅም፣ የጋራ እሴትና ማንነት ላይ ብሔራዊ መግባባት በፍጠር ከተቻለ ጠንካራ ሀገር በመገንባት ፈጣን ኢኮኖሚ ማስመዝገብ እንደሚቻል ገልጸው፣ ለዚህ መረባረብ ይኖርብናል ነው ያሉት።
ለዜጎች የሰላም አስፈላጊነትን በማስገንዘብ ትውልድ መገንባት ይኖርብናል ያሉት ሚኒስትሩ፣ ማህበራዊ ሀብታችንና ባህላዊ እሴቶቻችንን ለመገንባት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችን ሚና ማጉላት እንደሚገባ ገልጸዋል።