ዛሬ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
ዛሬ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ሰኔ 23/2015(ኢዜአ)፦ በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሁለተኛ ቀን ውሎ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።
በመርሐ-ግብሩ መሰረት አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ መድን ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አዳማ ከተማ በ37 ነጥብ 10ኛ ሲሆን ኢትዮጵያ መድን በ49 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አዳማ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ በሁለቱ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።
ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
ሌላኛው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ፋሲል ከነማን ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያገናኛል።
አስቀድሞ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ የያዘ ሲሆን ፋሲል ከነማ በ39 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዟል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአራቱ ሲሸነፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።
ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ በሁለቱ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።
ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ፋሲል ከነማ 2 ለ 1 ማሸነፉ ይታወሳል።
በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የ29ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ አርባ ምንጭ ከተማን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።