ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደቡብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 259 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ 

ጅንካ ፤ሰኔ 22/2015(ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ለተጎዱ ወገኖች  259 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ ድጋፍ አደረገ ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አሸብር ባልቻ ዛሬ በተካሄደው የድጋፍ ስነ ስርአት ላይ እንዳሉት ድጋፉ በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች፣ ኛንጋቶም፣ ሐመርና ሳላማጎ ወረዳዎች በድርቅና ተያያዥ ችግሮች ለተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎች የተደረገ ነው።

ድጋፉ 26 ሺህ 225 ኩንታል የቦቆሎ ዱቄት፣ 679 ኩንታል አልሚ ምግብ፣ 13 ሺህ 112 ኩንታል ባቄላ እና  87 ሺህ 418 ሊትር ዘይትን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ድጋፉ በወረዳዎቹ  ለ140 ሺህ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።

ከምግብ ድጋፍ ባሻገር በአካበቢው ድርቅን ለመቋቋምና የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚከናወኑ የመስኖ ልማት ስራዎችን ለመደገፍ 20 የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ድጋፍ መደረጉንም ስራ አስፈፃሚው አመልክተዋል።

ተቋሙ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በማሰብ ካለው አቅም ላይ በማካፈል ያደረገው የሰብአዊ ድጋፍ መሆኑን ጠቅሰው ድጋፉ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አማካኝነት እንደሚሰራጭም አስታውቀዋል ።


 

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበራ ቶላ በበኩላቸው ማህበሩ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩል የተደረገውን ድጋፍ  ለተጎጂዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልፀዋል ።

ማህበሩ በደቡብ ኦሞ ዞን በተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍ የተለያዩ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን ተናግረው በበጀት ዓመቱ ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሰብአዊ ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል።

በድጋፉ  ከ150 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

ከሰብአዊ ድጋፍ ባሻገር በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚሰሩ የውሃና ሌሎች መሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ኃላፊነቱን እየተወጣ  እንደሚገኝ አቶ አበራ አስታውቀዋል ።

የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ተወካይና የክልሉ አርብቶ አደር ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሎሬ ካኩታ መንግስት በድርቅና በጎርፍ አደጋ የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል ።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቋቋም ጎርፍ በሚያጠቃቸው አከባቢዎች የአረንጓዴ ልማትና የአፈርና ውሃ ዕቀባ እንዱሁም የመስኖ ልማትን የማስፋፋትና የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን  አቶ ሎሬ አስታውቀዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ በበኩላቸው ለተደረገው የሰብአዊ ድጋፍ በተጎጂዎች ስም አመስግነዋል ።

በዞኑ ወደ 400 ሺህ የሚጠጉ የማህበረሰብ ክፍሎች በድርቅና ተያያዥ ችግሮች ሳቢያ ለምግብ እጥረት እንደተጋለጡ ጠቁመው ዛሬ የተደረገው ድጋፍ ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረገውን ጥረት የሚደግፍ መሆኑን ገልጸዋል ።

በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች የታየውን የምግብ ክፍተት ለመሙላት የሚያስችል የመስኖ ልማት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው በአሁኑ ሰአት ከ4 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ እየለማ እንደሚገኝ  አቶ ንጋቱ አስታውቀዋል። ።

  በድጋፍ ቀጣይነትና ተጎጅዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ የተደረገ ጥናት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።

በድጋፍ ስነ ስርዓቱ ላይ የደቡብ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋምአን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም