ቀጥታ፡

የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ንቅናቄው የትምህርት መሰረተ ልማትን በማሟላት መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል - ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015(ኢዜአ)፡-በአገር አቀፍ ደረጃ የሚጀመረው የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ንቅናቄ፤ የትምህርት መሰረተ ልማትን በማሟላት ረገድ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ገለጹ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚካሔደው የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ ንቅናቄ ስኬት ሁሉም ዜጋ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ በመላው ሀገሪቱ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻል የሚደረገውን የንቅናቄ መርሃ ግብር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በቀጣዩ እሁድ በሚጀመረው የትምህርት ቤቶች ማሻሻያ የንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንደሚገኙም  ገልፀዋል።

በንቅናቄው በመላ አገሪቱ ከ50 ሺህ በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ እንደሚሰራም ነው የተናገሩት።

ንቅናቄው  ህብረተሰቡ በትምሕርት ተቋማት በተበታተነ መልኩ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ አገራዊና ወጥ በሆነ መልኩ ለማካሔድ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ትምህርት ቤቶችን የማሻሻል ብቻ ሳይሆን በማሕበረሰቡ ዘንድ የባለቤትነት ስሜትን የመፍጠር አላማ እንዳለውም አንስተዋል።

የትምህርት ጥራት ችግሮች ዘርፈ ብዙ ቢሆኑም  መሰረታዊ  ከሚባሉት ውስጥ ተቋማቱ ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ አለመሆን አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል።

ሚኒስቴሩ የትምህርት ቤቶችን ጥራት እንዴት እናሻሽል በሚል አራት ደረጃዎችን በማውጣት ጥናት ማካሔዱንም አንስተዋል።

በዚህ መሰረትም ለመማር ማስተማር ስራው ብቁ ሆነው አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የመንግስት ትምሕርት ቤቶች ከ0 ነጥብ 001 በመቶ በታች መሆናቸው በጥናቱ መረጋገጡን ጠቁመዋል።

10 በመቶ የሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ ከ89 በመቶ በላይ የሚሆኑት ለመማር ማስተማር ስራ ምቹ አለመሆናቸውን ገልፀዋል።

በመጪው እሁድ የሚጀመረው ንቅናቄም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ የታመነበት መሆኑን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ የትምህርት ተቋማትን በመንግስት አቅም ብቻ መልሶ ለመገንባት ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ እንደሚፈጅ አመልክተዋል።

በመሆኑም የትምህርት ቤቶችን ደረጃ የማሻሻል ስራ በህብረተሰቡ ትብብር መከናወን እንዳለበት አመላክተዋል።

ወላጆች፣ ባለሀብቶች እና በውጭ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለንቅናቄው ስኬት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት እንዲወጡም  ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም