የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመተግበር የአገልግሎት ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመተግበር የአገልግሎት ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ ይሰራል - የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015 (ኢዜአ)፡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሰራሽ አስተውሎት) በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመተግበር የአገልግሎት ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ያግዛል በተባለው በብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ግብዓት ለማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንዳሉት፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የሰው ልጅ እውቀትና ክህሎትን በመተካት ለችግሮች መፍትሔ የሚሰጥ ነው፡፡
የሰው ልጆች ድካማቸውን በመቀነስ በአይነትና በጥራት ምርታማ የሚያደርጋቸውን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ የምርምር ውጤቶችን በማቅረብ ለዘርፉ ማደግ አዎንታዊ ሚና የሚያበረክት ሥነ ምህዳር መገንባት የሚያስችል የፖሊሲ ዝግጅት ላይ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ በተመረጡ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር የዳታ አስተዳደር፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ህግና ሥነ ምግባር፣ ምርምርና ስርጸት፣ ትብብርና ቅንጅት ላይ በትኩረት ለመስራት ያስችላል ብለዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ፖሊሲው ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገና የወደፊት የልማትና ዕድገት አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሀገራዊ ሰነድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓተ ምህዳርን ማስፋት፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ማድረግ፣ እና መሰረተ ልማትና ሥርዓትን መገንባት የተቋሙ ተልዕኮ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ዝግጅትም የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረተ ልማትና ሥርዓት ግንባታ አንዱ አካል መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊሲው ኢትዮጵያ ያላትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሰረተ ልማት እና በዳታ ማዕከል ያለውን መረጃ ለሀገራዊ ጥቅም እንዴት ማዋል እንደሚገባ ወጥ አሰራር ለማስቀመጥ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሪ ዶክተር በአካል ግዛቸው፤ ኢትዮጵያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ገቢራዊ ለማድረግ የጀመረችው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የልህቀት ማዕከል እንድትሆን ካስፈለገ ዘርፉን በፖሊሲ መደገፍና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ ብሎም ሥነ ምህዳሩን ማስፋት ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡