ቀጥታ፡

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲና “ኢንቨስት አፍሪካ” የዩኬ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

 

አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015(ኢዜአ)፡- በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲና ኢንቨስት አፍሪካ የተሰኘው ግዙፉ የኢንቨስትመንት መድረክ የዩናይትድ ኪንግደም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ በጋራ ለመስራት ተስማሙ።

በዩናይትድ ኪንግደም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ አቶ በየነ ገብረመስቀል ከ”ኢንቨስት አፍሪካ” ዋና ስራ አስፈጻሚ ከረን ቴይለር ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኙ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ነዋያቸውን እንዲያፈሱ አስፈላጊውን ድጋፍ በጋራ ለማድረግ ተስማምተዋል።

ምክትል ሚሲዮን መሪው በኢትዮጵያ ያለውን ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ለማሳደግና ለማስተዋወቅ ኤምባሲው ከኢንቨስት አፍሪካ ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚፈልግ ተናግረዋል።

ሁለቱ አካላት ተቀራርበው መስራታቸው የጎላ ጠቀሜታ አለው ያሉት አቶ በየነ በተለይ በፈረንጆቹ 2024 በሚካሄደው የዩኬ-አፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ላይ ባለሀብቶች እንዲሳተፉ ለማገዝ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

የኢንቨስት አፍሪካ ዋና ስራ አስፈጻሚ ከረን ቴይለር በበኩላቸው በተለይ ለመጪው የዩኬ-አፍሪካ የኢንቨስትመንት ጉባኤ ስኬታማነት ሁለቱ አካላት ተቀራርበው መስራታቸው አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንቨስት አፍሪካ በተለይ በጉባኤው ተሳታፊ ለሚሆኑ የዩኬ ግዙፍ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ስላለው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የሚገልፅ ፕሮፖዛል ለማዘጋጀት ተስማምተዋል።

በተጨማሪም ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ካሉ የንግዱ ማህበረሰብና የመንግስት አካላት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ እንደሚያደርግ ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

ኢንቨስት አፍሪካ መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገና ከ400 በላይ ባለሀብቶችን ያቀፈ ግዙፍ የባለሀብቶች ስብስብ መሆኑን በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም