ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን ጋር ተወያይተዋል።
አቶ አክሊሉ ስለኢንዱስትሪ ፓርኮችና የድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ወቅታዊ መረጃዎችን በማቅረብ ቻይናውያን ባለሀብቶች በፓርኮቹና በነፃ የንግድ ቀጣና ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱም ኢትዮጵያ እና ቻይና ያላቸውን ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍም ማጠናከር እንዳለባቸው ዋና ስራ አስፈፃሚው ገልጸዋል።
መንግስት ለውጪና ለሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በፖሊሲና በማበረታቻዎች ላይ ያደረገውን ማሻሻያ በተመለከተም በዝርዝር አስረድተዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ቻይናና ኢትዮጵያ በፈተና ውስጥ ያልዋዠቀ ጠንካራ ወዳጅነትና ትብብር እንዳላቸው አንስተው ይህ ወንድማማችነት ከምንጊዜውም በበለጠ በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን በበኩላቸው በኢንቨስትመንትና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር የተጀመሩ ስራዎች አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
አምባሳደር ዣኦ ዥዩዋን አክለውም ኮርፖሬሽኑ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ሀገሪቱ የጀመረችውን የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዞ እውን ማድረግ የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከኮርፖሬሽኑ ጋር ከኢንቨስትመንት ባሻገር በትምህርትና ስልጠና በትብብር ለመስራት ኤምባሲው ዝግጁ መሆኑን አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ከኢንቨስትመንት፤ ከሰው ሀይል ስልጠናና ከትምህርት እድል በተጨማሪ በሌሎች የትብብር ማእቀፎች አብሮ ለመስራት መስማማታቸውን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።