ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ የባለ ድርሻ አካላት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ የባለ ድርሻ አካላት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015 (ኢዜአ):- በብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ የባለ ድርሻ አካላት የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ እንዳሉት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ከቀላል መዝናኛ ዘዴዎች እስከ ብሔራዊ ደህንነት የሰዎችን ሚና የሚተካ እና የሰዎችን ድካም በመቀነስ ጥራት እና ምርታማነትን የሚያሳድግ ቴክኖሎጂ ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ዓላማም 2022 ዓ.ም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የልህቀት ማዕከል ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የዘርፉ ምርምር ትኩረት በተመረጡ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ የዳታ አስተዳደር፣ የሰው ሀብት ልማት፣ ሕግና ስነ ምግባር፣ ምርምርና ስርጸት፣ ትብብርና ቅንጅት በስሩ የያዘ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ታዬ ግርማ ኢንስቲትዩቱ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የዘርፉን ስርዓተ ምህዳርን ማስፋት፣ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ማድረግ እና መሰረተ ልማት እና ስርዓትን መገንባት ተልዕኮ አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።
የብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ዝግጅትም የመሰረተ ልማትና ሥርዓት ግንባታ አንዱ አካል መሆኑን አመልክተዋል።