ቀጥታ፡

የመንግስት ተቋማት የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅን በአግባቡ ሊተገብሩ ይገባል-ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ


አርባ ምንጭ ሰኔ 22/2015(ኢዜአ):- የመንግስት ተቋማት በየደረጃው የሚስተዋለውን የሕግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅን በአግባቡ ሊተገብሩ ይገባል ሲሉ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2012 የፀደቀው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ ''የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶች እና ጥቅሞች የሚያስከትሉትን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ማረጋገጥ በማስፈለጉ'' የተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻል። 

የአስተዳደር ተቋማቱ ውሳኔ አሰጣጥ፣ የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ስነ-ስርዓት እንዲሁም አስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ስርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትሕ ማስፈን አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል።

የፍትሕ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ ለኢዜአ እንደገለጹት አዋጁ የዜጎችን መብት እና ጥቅም በማስከበር የሕግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር ለማስፈን ቁልፍ ሚና የሚጫወት ነው።

ይሁንና በአዋጁ ላይ በአስተዳደር አካላትም ሆነ በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ባለመኖሩና በአዋጁ መሰረት ስራዎች አለመከናወናቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈጠሩ ማድረጉን አመልክተዋል።

በመሆኑም የመንግስት ተቋማት በየደረጃው የሚስተዋለውን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለማቃለል አዋጁን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባ ተናግረዋል።

የፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁን እና አዋጁን ተከትሎ የወጡ መመሪያዎች ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ እና ግንዛቤ ለመፍጠር በትኩረት እየሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ የአዋጁን ተፈጻሚነት ለማረጋገጥ የክትትልና የኦዲት ስራ እያከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በበኩላቸው የሕግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር ሊሰፍን የሚችለው የመንግስት አስፈጻሚ አካላት በሕግ በተሰጣቸው የስልጣን ገደብ ሲሰሩ ነው ብለዋል።


 

ተግባራቸውን እና ኃላፊነታቸውን የሚያውቁ፣ በስነ-ምግባር እና በሕግ አግባብ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግስት ሰራተኞች መፍጠር ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

መብቱንና ግዴታውን የሚያውቅ ማህበረሰብ ለመፍጠር የግንዛቤ መፍጠር ስራ መከናወን አለበት ያሉት ዶክተር ዳንኤል ለዚህም የሚስተዋሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አዋጁ ስራ ላይ መዋሉ ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል።

የደቡብ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሶፎኒያስ ደስታ ባለ ጉዳዮችን በአግባቡ የማያስተናግዱና የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት የሚስተዋልባቸው ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጁ ተግባራዊ መሆን ለችግሮቹ መፈታት ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በክልሉ የተዘጋጀው የአስተዳደር ስነ-ስርዓት አዋጅ በቅርቡ በክልሉ ምክር ቤት ጸድቆ ስራ ላይ ይውላል  ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

በሕግ የበላይነት እና በመልካም አስተዳደር ግንባታ ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ የምክክር መድረክ ከሰሞኑ በአርባ ምንጭ ከተማ መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም