ከ838 ግራም በላይ የወርቅ ማዕድን ሲያሸሹና ህገ-ወጥ ጦር መሣሪያ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል-የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
ከ838 ግራም በላይ የወርቅ ማዕድን ሲያሸሹና ህገ-ወጥ ጦር መሣሪያ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል-የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22/2015(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦችና በጋምቤላ ክልሎች ከ838 ግራም በላይ የወርቅ ማዕድን ሲያሸሹና ህገ-ወጥ ጦር መሣሪያ ይዘው የተገኙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አስታውቋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቢሮ ወረዳና በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ 20 ክላሽንኮቭ ከ934 መሰል ጥይቶች ጋር፣ 8 ሽጉጥ ከ54 መሰል ጥይቶች ጋር፣ ሁለት ኤፍ ዋን ቦንቦች፣ አንድ GPS መያዙን ገልጿል።
በተጨማሪም 172 የተለያዩ የወርቅ ጌጣጌጦች፣ ከ838 ግራም በላይ የወርቅ ማዕድን፣ 7 የወርቅ ማቅለጫ ማሽኖች፣ 10 የወርቅ ሚዛን፣ ከ1 ሚሊዮን 653 ሺህ ብር በላይ በአሶሳ ዞን ኩምሩክ የፍተሻ ጣቢያ መያዙን ግብረ-ኃይሉ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት የማዕድን ግብይት አዋጅ ቁጥር 1144/2011 የተደነገገውን ክልከላ በመተላለፍ በሕገ-ወጥ መንገድ የወርቅ ማዕድን በማሸሽ ለግል ጥቅማቸው ለማዋል ሲሉ ግብረ-ኃይሉ ከህብረተሰቡ ባገኘው መረጃ መሠረት አሶሳ ዞን ኩምሩክ የፍተሻ ጣቢያ ባደረገው ፍተሻ መሆኑ ታውቋል።
በተጨማሪም በጣቢያው በተካሄደው ፍተሻ 20 ክላሽንኮቭ ጠመንጃ፤ ከ934 መሰል ጥይቶች ጋር እና ስምንት የተለያዩ ሽጉጦች ከ54 መሰል ጥይቶች ጋር፣ ሁለት ቦንቦች፣ አንድ ጂፒኤስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያን በመጣስ ከ1 ሚሊየን 653 ሺህ ብር በላይ ይዘው ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳዩ በምርመራ እየተጣራ መሆኑም ተገልጿል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ በመሰል የወንጀል ድርጊቶች የተሰማሩ ግለሰቦችና ቡድኖችን በማጋለጥ አሳልፎ ለፀጥታ አካላት በመስጠት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ግብረ-ኃይሉ ጥሪ ማቅረቡን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።