ቀጥታ፡

ከፕሪሚየር ሊጉ የሚወርደው ቀሪ አንድ ክለብ ሊለይበት የሚችልባቸው ወሳኝ የሊጉ ጨዋታዎች


አዲስ አበባ ሰኔ 22/2015 (ኢዜአ):- ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 29ኛ ሳምንት መርሐግብር ዛሬ በሚካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ወላይታ ድቻ ከወልቂጤ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንዲሁም አርባ ምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም በተመሳሳይ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፕሪሚየር ሊጉ የውድድር አመራር እና ስነ ስርዓት ኮሚቴ ሁለቱ ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰአት እንዲደረጉ ከትናንት በስቲያ ውሳኔ ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።

ጨዋታዎቹ ከሊጉ ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ያላቸው ወሳኝነት ከፍተኛ ነው።

ወላይታ ድቻ፣ አርባ ምንጭ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ ላለመውረድ እየተጫወቱ የሚገኙ ክለቦች ናቸው። 

በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የሚደረገው ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ወልቂጤ ከተማን ያገናኛል።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ወላይታ ድቻ በ36 ነጥብ 11ኛ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ በ33 ነጥብ 14ተኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ወላይታ ድቻ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በሁለቱ ሲሸነፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ወልቂጤ ከተማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአንዱ አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሌላኛው ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ አርባ ምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ የሚያደርጉት ነው።

በደረጃ ሰንጠረዡ አርባ ምንጭ ከተማ በ33 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ በ36 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።

አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ሲያሸንፍ በሶስቱ ተሸንፏል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማ 3 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ  ከሊጉ አስቀድመው መውረዳቸውን ያረጋገጡ ክለቦች መሆናቸው ይታወቃል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ ሰኔ 25 ቀን 2015 ይቆያል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም