ቀጥታ፡

በዓሉ ሲከበር ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ ወገኖች ካለን በማካፈል በአብሮነት መሆን አለበት---ሸህ መሀመድ አንዋር 

ባህር ዳር  ሰኔ 21/2015 (ኢዜአ)፡- ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ ወገኖች ያለውን በማካፈል በዓሉን በአብሮነት ማክበር እንዳለበት የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሸህ መሀመድ አንዋር ገለጹ።

1ሺህ 444ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በድምቀት ተከብሯል።

የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሸህ መሀመድ አንዋር በእዚህ ወቅት እንዳሉት አረፋ የእኩልነት፣ የፍትህና የአብሮነት በዓል ነው።

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ያለውን ለተፈናቀሉና ለተቸገሩ ወገኖቹ በማካፈል በዓሉን በአብሮነትና በደስታ ማክበር እንዳለበት አመልክተዋል።

ለእዚህም የእምነቱ አስተምህሮ በሚያዘው መሰረት ከእንስሳት እርድ አንድ ሦስተኛውን ለችግረኞች በማካፈል የማስደሰት ሃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሳህሉ በበኩላቸው ከተማዋ ሙስሊሙና ክርስቲያኑ ተሳስበውና ተከባብረው የሚኖርባት  ናት።

በሁሉም ሃይማኖት አስተምሮው ሰላም ትልቅ ቦታ እንዳለው አስታውሰው፣ ሁሉም ለሀገራዊ አንድነት፣ ለሰላም ና ልማት  አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ችግሮች ሲከሰቱም በውይይትና በመነጋገር በመፍታት ለዘመናት የዘለቀውን የህዝቦች አንድነት ማጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

"የኢድ አል አድሃ በዓል የመተሳሰብና ከራስ ባለፈ ለሌሎች ደስታን የምናጋራበት ነው" ያሉት ደግሞ የበዓሉ ተሳታፊ ረዳት ፕሮፌሰር ምርታቸው ጣሂር ናቸው።

በዓሉን በመተሳሰብና በመተጋገዝ ከማሳለፍ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጋራ ጠላት የሆነውን ድህነት በጋራ ለመዋጋት ቃል የምንገባበት መሆን አለበት ብለዋል።

የጥንቱን የመተሳሰብና የመከባበር እሴት በማጎልበት በዓሉን እያከበሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ሀጂ ተዘራ አበበ ናቸው።

ለቀጣዩ ትውልድ የለማች ኢትዮጵያን ለማስተላለፍ እየተደረገ ባለው ጥረት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሲያደርግ የነበረውን ንቁ ተሳትፎ በቀጣይም ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በባህር ዳር ከተማ ዛሬ በድምቀት በተከበረው የአረፋ በዓል ላይ የሃይማኖቱ አባቶች፣ በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት ተገኝተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም