ቀጥታ፡

ዒድ አል አደሃ (አረፋ) ታዛዥነትንና ታማኝነትን የምንማርበት ታላቅ በዓል ነው - ዑስታዝ አቡበከር አህመድ

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015 (ኢዜአ) ፡- ዒድ አል አደሃ (አረፋ) ታዛዥነትን እና ታማኝነትን የምንማርበት ታላቅ በዓል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ልዩ አማካሪ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ ገለጹ።

1ሺህ 444ኛው የዒድ አል አድሃ በዓል በአዲስ አበባ እና ሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተከብሯል።

ዒድ አል አድሃ (አረፋ) አላህ (ሱብሀነሁ ወተአላ) ነቢዩ ኢብራሂምን፣ ልጅህን መሥዋዕት አድርግልኝ ብሎ ሲያዛቸው፣ ልጃቸውን እስማኤልን መሥዋዕት ለማድረግ የተነሡበት በዓል ነው፡፡

የአረፋ በዓል ከአምስቱ የእስልምና መሠረቶች መካከል ማንኛውም ሙስሊም በሕይወት ዘመኑ ቢያንስ አንዴ ወደ መካ በመጓዝ እንዲያከናውነው የሚጠበቅበት የሐጅ ሥርዓት የሚካሄድበትና የሚጠቃለልበት ታላቅ ምዕራፍ ነው፡፡ 

በዓሉ የመተሳሰብና የመረዳዳት ሃይማኖታዊ እሴት የሚንጸባረቅበት ነው።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ልዩ አማካሪ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በዓሉ ነብዩ ኢብራሒም ለፈጣሪ ያሳዩትን መታዘዝ የምንተገብርብትና የምናስብበት ነው።

ሰዎች ለፈጣሪ ያላቸውን ታዛዥነት እና ታማኝነት የሚያሳዩበት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

በመሆኑም የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን በመረዳዳትና መተሳሰብ ማሳለፍ እንዳለባቸው ገልጸዋል። 

አቅመ ደካሞችን እና ችግረኞችን ከጎናቸው በመቆም አዲስ የህይወት ምዕራፍ የሚፈጥሩበት እና ከፈጣሪ ጋርም ቃል የሚገባበት መሆኑን አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም