የመተባበር እና መተጋገዝ እሴትን የዘወትር በጎ ተግባር ማድረግ ያስፈልጋል - ሼህ ሱልጣን አማን - ኢዜአ አማርኛ
የመተባበር እና መተጋገዝ እሴትን የዘወትር በጎ ተግባር ማድረግ ያስፈልጋል - ሼህ ሱልጣን አማን
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015 (ኢዜአ)፡- በበዓላት ወቅት የሚደረጉ የመተባበር እና መተጋገዝ እሴቶችን የዘወትር በጎ ተግባር ማድረግ እንደሚያስፈልግ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን አማን ገለጹ።
1ሺህ 444ኛው የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል በመዲናዋ አዲስ አበባ እና በሌሎች ኢትዮጵያ አካባቢዎች በሶላት፣ ተክቢራ እና ሌሎች ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች በድምቀት ተከብሯል።
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሱልጣን አማን እንዳሉት አቅም ደካማና የተቸገሩ ወገኖችን ማገዝ የኢድ በዓል ከሚያስተምራቸው መልካም ነገሮች አንዱ ነው ብለዋል።
ህዝበ ሙስሊሙም በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ እና አቅም ደካማ ወገኖች በማገዝ ሊሆን እንደሚገባም ነው የገለጹት።
በበዓሉ ከሚከናወነው የእርድ ሥርዓትም ለድሆች፣ አቅመ ደካሞች እና ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
ህዝበ ሙስሊሙም የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን በመተባበር፣ መተጋገዝ እና በመተሳሰብ በማሳለፍ ኃማኖታዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በበዓላት ወቅት የሚከናወኑ የመተዛዘን፣ የመተሳሰብና የመከባበር መልካም እሴቶች የዘወትር ተግባር ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአላት ሲከበሩ ከተቸገሩ እና ከአቅመ ደካማ ወገኖች ጋር ማሳለፍ የእምነቱ ግዴታ መሆኑን ጠቁመው፤ ዜጎችም የመተባበር እና የአጋርነትን ቀና ተግባራትን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
ኢዜአ ካነጋገራቸው የበዓሉ ተሳታፊ መካከል ዑስታዝ በድሩ ሁሴን እንዳሉት የተቸገረን ማሰብ እና ማገዝ ከፈጣሪ ዘንድ ትልቅ ትሩፋት የሚያስገኝ መልካም ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
በበአሉ ወቅት ከሚደረጉ እርዶች አንድ ሶስተኛው ለተቸገሩ ወገኖች የሚሰጥበት መሆኑን አንስተው፤ ይህም በዓሉን ስናሳልፍ መልካምነት እና ደግነት በመላበስ መተሳሰብ የግድ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
መተባበርና መተጋገዝ የእምነቱ እና የበዓሉ መሰረቶች በመሆናቸው በዓሉን በመረዳዳት እናሳልፋለን ያሉት ደግሞ ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ አባድር ዱላ ናቸው።