ቀጥታ፡

የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎችን እውቀትና ብቃት ለመለካት የሚሰጠው የመውጫ ፈተና ዝግጅት ተጠናቋል-ትምህርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015 (ኢዜአ) የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎችን እውቀትና ብቃት ለመለካት የሚሰጠው የመውጫ ፈተና ዝግጅት መጠናቀቁን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል አንዱ ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ተደራሽ የማድረግ ግብን ለማሳካት እየሰራች ነው።

እንደ አገር በትምህርት ተደራሽነት ላይ ባለፉት 25 ዓመታት በስፋት ቢሰራም በጥራት በኩል ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በመረጋገጡ ይህን ማሻሻል የሚያስችል የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን እንዲያስመርቁና የትምህርት ጥራታቸውን እንዲያሻሽሉ እየተሰራ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።

ይህን ጉዳይ በማስመልከት በትምህርት ሚኒስቴር የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ኢዮብ አየነው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በዚህም በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ራስ ገዝ የማድረግ፣ በተልዕኮ የመለየት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን መረጃ በአንድ የዲጂታል ማዕከል ማስተዳደር እና የመውጫ ፈተና መስጠትን ማዕከል ያደረጉ የለውጥ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።

በዚህም ዘንድሮ የሚመረቁ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውንና በተማሩበት ሙያ አጠቃላይ መሰረታዊ እውቀት ስለመጨበጣቸው የብቃት መለኪያ በማዘጋጀት የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ ይደረጋል ነው ያሉት።

የመውጫ ፈተና ለዩኒቨርሲቲዎች አዲስ እንዳልሆነ የገለጹት ኃላፊው፤ የህግ እና የጤና ተማሪዎች ከ10 ዓመታት በላይ የመውጫ ፈተና ሲወስዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ያንን ልምድ በማስፋትና እንደ ሀገር ገበያው የሚፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት የመውጫ ፈተናው ከ2015 ጀምሮ በሁሉም የትምህርት መስኮችና መርሐ ግብሮች መስጠት እንዲቻል ስራዎች ከአንድ ዓመት በላይ ሲሰሩ ቆይተዋል ነው ያሉት።

ፈተናውም ከሃምሌ ሶስት እስከ ስምንት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋ።

ስለፈተናው ለተማሪዎችና ለትምህርት ማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራታቸውን እና ምክክር ሲደረግ መቆየቱንም ጠቅሰዋል።

ተማሪዎች በትምህርት ቆይታቸው ከተማሯቸው የትምህርት ዓይነቶች መካከል መሰረታዊ የሚባሉ ከ12 እስከ 17 የትምህርት ዓይነቶች ፈተና እንደሚወጣ ገልጸው፤ ለዚህም የፈተና ንድፍ እና የብቃት መመዘኛ መስፈርቶች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በመውጫ ፈተና አዘገጃጀት መመሪያ መሰረትም ከግንቦት 15 ጀምሮ ለ211 የትምህርት ፕሮግራሞች የፈተና ጥያቄዎች በማውጣት ለፈተናው ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል ነው ያሉት።

ፈተናው በኦንላይን የሚሰጥ በመሆኑም አስፈላጊ የቴሌኮም እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሀገሪቱ ካሉ 325 የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 161 እና ከመንግስት ደግሞ 44 ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን እንደሚያስፈትኑ ጠቅሰዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን የትክክለኛ ተፈታኞችን ቁጥር እንዲያጣራ በማድረግ፤ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 95 ሺህ 755 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ 74 ሺህ 706 ተማሪዎች ለፈተና እንደሚቀመጡ ጠቁመዋል።

ፈተናውን ያላለፉ ተማሪዎቸ ዲግሪ እንደማይሰጣቸው እና የትምህርት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው የፈተና ጊዜ መሰረት ድጋሚ እንደሚፈተኑ ተናገረዋል።

ፈተናው ለበርካታ ተማሪዎች አዲስ ቢሆንም የዓመታት ልፋታቸውንና የገበዩትን እውቀት የሚለካ መሆኑን በመገንዘብ በተረጋጋ ሁኔታ ለመፈተን እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።

ወላጆችም ልጆቻቸው ብቁ ሆነው እንዲመረቁላቸው በስነ-ልቦና ማገዝ እንዳለባቸው ነው ዶክተር ኢዮብ የጠየቁት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም