ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የሰፈነውን ሰላም ለማጽናት እና አንድነታችን ለማስጠበቅ የዜግነት ኃላፊነታችንን እንወጣለን--የእስልምና እምነት ተከታዮች

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ የሰፈነውን ሰላም ለማጽናት እና የሀገር አንድነትን ለማስጠበቅ የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።

1 ሺህ 444ኛው የዒድ አል አደሃ (አረፋ) በዓል በአዲስ አበባ ስቴዲየም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በተለያዩ ስነ-ስርዓቶች በድምቀት ተከብሯል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ያነጋገራቸው የበዓሉ ተሳታፊዎች የአረፋ በዓልን ስናከብር አቅመ ደካሞችን በማገዝና በመተሳሰብ ሊሆን የገባል ብለዋል።

በበዓሉ አከባበር ላይ ያገኘናቸው ኑር ደዊሸፍ እንዳሉት፣ በዓሉን እርስ በርስ በመረዳዳት ከማክበር ባለፈ የሀገርን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ መስራት ተገቢ ነው።

ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን እና የአካባቢውን ሰላም በማረጋገጥ በኩል ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለሁሉም የምትመች እና የበለጸገች ሀገር እንድትሆን ሰላሟን በአስተማማኝ ሁኔታ ማስፈን እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አብዱልቃድር ድላላ ናቸው፡፡


 

"ኢትዮጵያ ነብዩ መሐመድ ዱዓ ያደረጉላት ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያን አትንኩ ሲሉ የተናገሩላት አገር ናት እናም እኛ የዚህ ዘመን ትውልዶች ለሰላሟ መስፈን ግንባር ቀደም ሆነን መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል፡፡


 

ሃጂ ኢብራሔም አሊ በበኩላቸው  ሁላችንም ከዘረኝነትና ከመከፋፈል ወጥተን አንድነታችንን ልናስጠበቅ ይገባል ነው ያሉት።

ጠንካራና ለሁሉም የምትመች ሀገርን ለመገንባት ከሌሎች  የእምነት ተከታዮች ጋር በአብሮነት መንፈስ ለሀገራችን ሰላም በጋራ እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም