የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የምግብ ጥራትና ደህንነት ምርመራ ላቦራቶሪ የአክሪዲቴሽን እውቅና አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የምግብ ጥራትና ደህንነት ምርመራ ላቦራቶሪ የአክሪዲቴሽን እውቅና አገኘ
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት ለኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን የምግብ ጥራትና ደህንነት ምርመራ ላቦራቶሪ የአክሬዲቴሽን እውቅና ሰጥቷል።
የምግብ ላቦራቶሪው እውቅና ያገኘው በዓለም አቀፍ በተቀመጡ ዝርዝር መስፈርቶች መሰረት በተደረገ ግምግማ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ አክሪዲቴሽን አገልግሎት እውቅናውን ተረክቧል።
በእውቅና መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ላቦራቶሪው ዘመኑ የደረሰባቸው መሳሪያዎች የማደራጀት፣ አስፈላጊውን ግብዓቶች የማሟላት እና ስራው ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን የማብቃት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ዶክተር ሊያ ታደሰ አክለውም የምግብን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ ከሚያስችሉ ዋነኛ መሳሪያዎች መካከል አንዱ ላቦራቶሪ መሆኑንም ገልጸዋል።
ባለስልጣኑ የሚጠበቅበትን መስፈርቶች አሟልቶ እውቅናውን እንዲያገኝ አስተዋጽኦ ላደረጉ ድርጅቶች፣ ተቋማት፣ የስራ ክፍሎች እና ግለሰቦች የምስጋና ምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።