ቀጥታ፡

የጸጥታ አካላት ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መረጋገጥ በትኩረት ሊሰሩ ይገባል   -   የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን

አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015 (ኢዜአ) የጸጥታ አካላት ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መረጋገጥ ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳሰበ።

ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጣቢያዎች እና በተጠርጣሪዎች ማቆያ ያለውን የሰብዓዊ መብት አያያዝ ምልከታ አድርጓል፡፡

ኮሚሽኑ በህገ- መንግስቱ እና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ተፈጻሚነትን ክትትል አድርጓል።

በአካል ምልከታ፣ የተለያዩ ሰነዶችን በመመልከት፣ከታራሚዎች እና ከማረሚያ ቤቶች አመራሮች ጋር በተደረጉ ቃለመጠይቆች እና ውይይቶች መረጃ ማደራጀቱን ገልጿል።

ክትትሉ በ 15 ዞኖች በሚገኙ 118 ፓሊስ ጣቢያዎች እና ሁለት የታራሚ ማቆያዎች ላይ መደረጉ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶክተር አብዲ ጂብሪል በዚሁ ወቅት እንዳሉት ፖሊስ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር በሚሰራቸው ስራዎች ላይ የአፈጻጸም ውስንነቶች እንደሚስተዋሉ ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎችን በ 48 ሰአት ውስጥ ፍርድ ቤት የማቅረብ፣ የፍርድ ቤት ትእዛዝን የማክበር እንዲሁም ተጠርጣሪዎች የተያዙበትን ምክንያት የማወቅ መብታቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል።

ስለዚህም ጸጥታ አካላት ለዜጎች ሰብአዊ መብት መረጋገጥ ይበልጥ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ዶክተር አብዲ ጂብሪል ያስገነዘቡት።
 

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እና የምርመራ ዘርፍ ሀላፊ ዘሪሁን ዱጉማ በበኩላቸው በኮሚሽኑ የተነሱ አንዳንድ ውስንነቶች ቀደም ብለው በግምገማም የተለዩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ችግሮቹን በመለየት የመፍትሄ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውን ተናግረዋል።

ግኝቶቹ እነዚህን የመፍትሄ አቅጣጫዎች በማጠናከር ወደፊት የሰብዓዊ መብትን ለማሻሻል ለሚከናወኑ ስራዎች ግብአት እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያስመዘገባቸው መልካም ጅምሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።

የክልሉ የሰላም እና ፍትህ ክላስተር ጽህፈት ቤት ሃላፊ ጌታቸው ታምራት የሰብዓዊ መብት አያያዝን ለማሻሻል የፍትህ ማሻሻያ ስርዓት መተግበር መጀመሩን መገልጸዋል።

ይህን ተከትሎ በየደረጃው ባሉ የፍትህ ማሻሻያ ኮሚቴዎች አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው ለተፈጻሚነቱ በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም