ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገርን እድገትና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገርን እድገትና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገርን እድገትና የዜጎችን ኑሮ ማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።
ኢትዮ-ቴሌኮም እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመተባበር ፈጣን እና ቀላል በሆነ አማራጭ ተግባራዊ የሚደረጉ የፋይናንስ አገልግሎቶችን ይፋ አድርገዋል።
ይፋ የሆኑት በቴሌብር አማካኝነት በሞባይል ተግባራዊ የሚደረጉት አራት የፋይናንስ አገልግሎቶች መሆናቸው ተጠቁሟል።
እነዚህም ድልድይ፣ እንደራስ፣ ስንቅ እና አድራሽ የተባሉ ሲሆን፤ ደንበኞች ገንዘብ መያዝ ሳይጠበቅባቸው ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ገንዘብ የሚቆጥቡበትና የሚበደሩበት ነው።
የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚህ ወቅት ተቋሙ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለአገር እድገት ወሳኝ የሆኑና የዜጎችን ህይወት ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ስልክን ከመደበኛ አገልግሎት በተጨማሪ ለሌሎች የዲጂታል አገልግሎት እንዲውሉ ሰፊ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
የፋይናንስ አገልግሎቱ ደንበኞች ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም ለግለሰቦች፣ በንግድ ስራ ለተሰማሩ ተቋማት፣ ህጋዊ ለሆኑ ወኪሎችና ለአነስተኛ ቁጠባና ብድር አገልግሎት ሰጪዎች ገንዘብ የሚቆጥቡበት፣ የሚበደሩበትና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ነው።
እንደ አገር ዘላቂ የሆነ ዕድገት ለማምጣትና ድህነትን ለማሸነፍ አካታች የሆነ ስርዓት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ዲጂታል ፋይንናስ አገልግሎት ወሳኝ ሚና እንዳለው ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው ባንኩ የዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጮችን በማቅረብ በኩል ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
ደንበኞቹ በተያዘው ዓመት አብዛኛው የገንዘብ ዝውውር የፈጸሙት በዲጂታል አገልግሎቶች በኩል መሆኑን ገልጸዋል።
አገርን ለማሳደግ በጋራ መስራት አስፈላጊ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር የቀረቡት አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶች፤ ባንኩ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮ-ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመተባበር ካስጀመሯቸው አራት አገልግሎቶች ውስጥ 'ስንቅ' ከወለድ ነጻ ወይም ወለድ የሚታሰብበት የቁጠባ አገልግሎት ነው።
እንዲሁም 'እንደራስ 'አነስተኛ ብድር ለማግኘት የሚያስችል፣ 'ድልድይ 'አነስተኛ የንግድ ወይም ቢዝነስ ለመጀመር ወይም ለማስፋፋት የሚያስችልና 'አድራሽ' ወርሃዊ ደመወዝ በቴሌብር ለሚከፈላቸው የደመወዝ ማድረሻ ብድር የሚያገኙበት አገልግሎቶች ናቸው።
በፋይናንስ አገልግሎቶች ይፋ ማድረጊያ ስነ-ስርዓት ላይ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ ሰለሞን ደስታን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።