የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያቸው የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ የጤና ተቋማት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያቸው የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ሰኔ 21 / 2015 (ኢዜአ) የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአማራ እና አፋር ክልሎች ለሚገኙ 22 የጤና ተቋማት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ ።
የሕክምና ቁሳቁሶቹን በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አወር የጀርመን መንግሥት የልማትና ኢኮኖሚ የትብብር ሚኒስቴር ኃላፊዎችና በጀርመን የባቫሪያ ግዛት ተወካዮች በተገኙበት ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።
ድጋፉ በሰሜን የኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት በአማራ እና አፋር ክልሎች ጉዳት ለደረሰባቸው 12 ሆስፒታሎች እና 10 ጤና ጣቢያዎች እንደሚውል ተገልጿል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፤ ድጋፉ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የህክምና ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና የአገልግሎት አድማሳቸውን ለማስፋት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በቀጣይ በትግራይ መልሶ ግንባታ እንዲሁም በሌሎችም በግጭትና በድርቅ የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ማቋቋም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።
የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን አወር በበኩላቸው የጀርመን ፌዴራል መንግሥት እና የባቫሪያ ግዛት በመልሶ ማቋቋምና የጤና አገልግሎትን ለማሻሻል ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን በጠንካራ አጋርነት እንደሚቆሙ ተናግረዋል።
ዛሬ የተደረገው ድጋፍ የቀዶ ጥገና መሳሪያዎች፣ የጽኑ ሕሙማን ማከሚያ ማሽኖች፣ የማዋላጃ መሳሪያዎች፣ የላብራቶሪ እቃዎች እና የአስተኝቶ ማከሚያ መሳሪያዎችን መሆኑን ጠቅሰው።
ድጋፉ በግጭት የተጎዱ የጤና ተቋማትን በማገዝ ለአካባቢው ህብረተሰብ በቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ነው ብለዋል።
የጀርመን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አምባሳደሩ ጠቁመዋል።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የክብር አምባሳደር ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል።