የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ተጠየቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2015(ኢዜአ)፦ የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ።
ጃፓን በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት(ዩኒዶ) ጋር በመተባበር ያዘጋጁት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በቶኪዮ አካሄዷል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ የኢትዮጵያ እና ጃፓን ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስታውሰዋል።
ይህን ግንኙነት ይበልጥ ለማሳደግ በተለይም ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር አውደ ጥናቱ የራሱ አበርክቶ እንዳለው አመልክተዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፈጣን ዕድገት ላይ ይገኛል ያሉት አምባሳደሩ ይህን ዕድል በሙሉ አቅም ለመጠቀም መንግስት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም በማካሄድ አስቻይ የቢዝነስና ኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን መፍጠሩን ገልጸዋል።
የጃፓን ኩባንያዎች ይህንኑ አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት መስኮች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ መሰማራት የሚያስችላቸው ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን አመልክተዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የኢንቨስትመንት ዘርፍ መሪዎች መሳተፋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።