ለሸኔ የሽብር ቡድን የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
ለሸኔ የሽብር ቡድን የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2015(ኢዜአ)፦ ለሸኔ የሽብር ቡድን የትጥቅ ድጋፍ ለማድረግ ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት ሰኔ 20 ቀን 2015 ዓ.ም መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ለቡ አድርገው የሠሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2-አአ B25609 በሆነ ቶዮታ ኮሮላ መኪና አንድ ብሬን እና 263 የክላሽንኮቭ
ጥይቶችን ጭነው ሲጓዙ እንደሆነ ግብረ ኃይሉ ገልጿል።
ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ሆለታ ከተማን እንዳለፉ በፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል በተደረገ ጠንካራ ክትትል መሆኑንም አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከህገ-ወጥ የጦር መሣሪያው በተጨማሪ ለእኩይ ዓለማቸው ማስፈፀሚያ ሐሰተኛ የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የልደት ምስክር ወረቀት፣ ልዩ ልዩ ማህተሞች እና ሀሰተኛ ሰነዶችን መያዛቸውንም ነው ግብረ ሀይሉ የገለጸው።
ተጠርጣሪዎቹም በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በምርመራ እየተጣራ እንደሚገኝም ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
ኅብረተሰቡም እነዚህ ህገ-ወጥ መሣሪያዎች በሸኔ የሽብር ቡድን እጅ ቢገቡ ኖሮ በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝቦ መሰል የወንጀል ተግባራትን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረ ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።