የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ወደ 53 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ አድርጎታል - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ወደ 53 ነጥብ 5 በመቶ ከፍ አድርጎታል - ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ የነበረውን የአምራች ኢንዱስትሪ የማምረት አቅም ከ53 ነጥብ 5 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ገለጹ።
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት 'በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ' በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ የተፈጠረውን መነቃቃት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገር በፈተናዎች ውስጥ በነበረችበት 2014 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለመፍጠር አምራች ኢንዱስትሪውን ማጎልበት አማራጭ የሌለው በመሆኑ የተጀመረ ንቅናቄ መሆኑንም ገልጸዋል።
በንቅናቄው የመጀመሪያው ምዕራፍ ከዘርፉ ውስብስብ ችግሮች አኳያ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ጉዞ ለመምራት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኮቪድ 19፣ ጦርነትና ዓለም አቀፍ ፈተናዎች እያሉ የአምራች ኢንዱስትሪው የማምረት አቅም ከ2012 ዓ.ም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 53 ነጥብ 5 መቶ እንዲያደግ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በአስር ዓመቱ መሪ ልማት እቅድ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ የማድረግ ግብ መያዙንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ፈተናዎችና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖዎችን ተቋቁማ የአምራች ኢንዱስትሪውን ዘርፍ የማምረት አቅም ከነበረበት ዝቅተኛ አፈፃፀም ማሳደግ መቻሏን ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የጎላ አበርክቶ እንደነበረው አስታውሰው፤ ንቅናቄው የአንድ ወቅት ዘመቻ ሳይሆን የአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ አካል ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ንቅናቄው ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመው የነበሩ 352 ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ ከማስገባት ባለፈ 653 አዳዲስ አምራች ኢንዱስትሪዎች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ አስችሏል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች የውድድር፣ ፉክክርና ትብብር መንፈስ መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈተናዎችን ውስጥም ሆና ለአምራች ኢንዱስትሪው ተመራጭ ሀገር መሆኗን ባለፉት ዓመታት አሳይታለች ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለመፍጠር ምርታማነትን ማሳደግ ለነገ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡
መንግስት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በብድር ከሰጠው 434 ቢሊዬን ብር 12 በመቶ የሚሆነው ለአምራች ኢንዱስትሪው የተሰጠ ቢሆንም ከዚህ በላይ ማደግ ይገባዋልም ብለዋል፡፡