የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ አራት አይነት አዳዲስ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ይፋ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ አራት አይነት አዳዲስ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ይፋ አደረጉ
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ በመሆን በቴሌብር አማካኝነት ለህብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደርጓቸውን አራት አይነት የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ይፋ አደረጉ፡፡
በዛሬው እለት ይፋ የሆኑት አገልግሎቶች ድልድይ፣ እንደራስ፣ ስንቅ እና አድራሽ የተባሉ የሞባይል ገንዘብ ማንቀሰሳቃሻ አገልግሎቶች ናቸው።
በአገልግሎቶቹም ደንበኞች ገንዘብ በካሽ መያዝ ሳይጠበቅባቸው ተንቀሳቃሽ ስልካቸውን በመጠቀም ግለሰቦች፣ በንግድ ስራ ለተሰማሩ ተቋማት፣ ህጋዊ ለሆኑ ወኪሎችና አነስተኛ ቁጠባና ብድር አገልግሎት ሰጪዎች ገንዘብ የሚቆጥቡበት፣ የሚበደሩበትና አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት ነው።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት ይህ አገልግሎት ማህበረሰቡ ቀልጣፋ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል ነው።
አገልግሎቶቹም ለዲጅታል ኢኮኖሚ ሽግግር የሚደረገውን ጥረት አጋዥ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ አገልግሎቱ አካታችነት ያለውና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የባንኩ የዲጅታል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህም ደንበኞቹን በቀላሉ ተደራሽ ለመሆን እንደሚያስችለው ተናግረዋል፡፡