ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት ተችሏል- አቶ መላኩ አለበል 

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ገለጹ። 

ሚኒስትሩ ይህን ያሉት 'በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ' የአምራች ኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ዙሪያ በሰጡት  መግለጫ ነው።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሀገር በፈተናዎች ውስጥ በነበረችበት 2014 ዓ.ም መጀመሩን አስታውሰዋል።

በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ለመፍጠር አምራች ኢንዱስትሪውን ማጎልበት አማራጭ ባለመኖሩ የተጀመረ ንቅናቄ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በንቅናቄው የመጀመሪያው ምዕራፍ ከዘርፉ ውስብስብ ችግሮች አኳያ ቀሪ ስራዎች ቢኖሩም ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገውን ጉዞ ለመምራት ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ መዋቅሮች የውድድር፣ ፉክክርና ትብብር መንፈስ ገቢራዊ የተደረገ መሆኑንም አውስተዋል። 

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኮቪድ 19፣ ጦርነትና ዓለም አቀፍ ፈተናዎች እያሉ የአምራች ኢንዱስትሪው የማምረት አቅም ከ2012 ዓ.ም ከነበረበት 46 በመቶ ወደ 50 መቶ እንዲያደግ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ንቅናቄው ሙሉ በሙሉ ስራ አቁመው የነበሩ 352 ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ ማስቻሉንም እንዲሁ።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም