የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስከበርና የባህር ኃይል ስሟን ዳግም ከፍ አድርጎ ለማስጠራት ዝግጁ ነን- የኢትዮጵያ ባህር ኃይል መሰረታዊ ባህረኞች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስከበርና የባህር ኃይል ስሟን ዳግም ከፍ አድርጎ ለማስጠራት ዝግጁ ነን- የኢትዮጵያ ባህር ኃይል መሰረታዊ ባህረኞች
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ክብር እና ሉዓላዊነት ለማስከበርና የባህር ኃይል ስሟን ዳግም ከፍ አድርጎ ለማስጠራት ዝግጁ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ባህር ኃይል መሰረታዊ ባህረኞች አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ባህር ኃይል እንደ አዲስ ከተቋቋመ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በተለያዩ ሙያዎች ያሰጠለናቸውን መሰረታዊ ባህረኞች ዛሬ በቢሾፍቱ አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ ላለፉት ሁለት ዓመታት በ'ናቪጌሽን'፣ በመርከብ ደህንነት፣ በኤሌክትሪክና ኮምዩኒኬሽንና ሌሎችም መስኮች የሰለጠኑ ናቸው ብለዋል።
ዛሬ ከተመረቁ ባህረኞች መካከል የዋንጫ ተሸላሚው መሰረታዊ ባህረኛ መንግሥቱ አበበ በባህር ኃይል መስክ የንድፈ ሀሳብ የተግባርና የአካል ብቃት ስልጠናዎችን በመውሰድ ለማንኛውም ብሔራዊ ግዳጅ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጠንካራ የባህር ኃይል እንደነበራት በማስታወስ፥ ከረጅም ዓመታት በኋላ እንደ አዲስ የባህር ኃይል መቋቋሙም ትልቅ ውሳኔ መሆኑን ተናግሯል።
መሰረታዊ ባህረኛ ፋሲል ፍስሐ በበኩሉ "ገናናውን የባህር ኃይል ትንሳኤ ለማረጋገጥ በተጀመረው ሂደት አሻራውን ለማሳረፍ ተመልምሎ በመሰልጠኑና የመጀመሪያው ምሩቅ ደስተኛ ነኝ" ብሏል።
የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በትጥቅ እና በብቁ ሙያተኛ የተደራጀ እንደነበር አስታውሶ በወሰዱት ስልጠናም ያንን ስም ዳግም ለመትከል የሚያስችል ሁለገብ እውቀት አግኝቻለሁ ሲል ገልጿል።
መሰረታዊ ባህረኛ አንጓች ባዩ እና ምስር መኩሪያ በበኩላቸው፤ የወሰዱት ስልጠና ሁለገብ እና በቀጣይ የሚሰጠንን ግዳጅ ለመወጣት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የባህር ኃይል ዳግም መመስረቱን ተከትሎ ኢትዮጵያን ለማኩራት የታሪክ ባለ አደራ ሆኖ በመመረቁ ኩራት ይሰማኛል ያለው ደግሞ መሰረታዊ ባህረኛ እዩኤል መታገስ ነው።
በፅናትና በቆራጥነት አገራቸውን ለማኩራት እንሰራለን ያሉት ተመራቂዎቹ በተሰማሩበት የባህር ኃይል "የኢትዮጵያን ጥቅሟንና ብሔራዊ ክብሯን ለማስጠበቅ የትኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን" ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ቀድሞ በአፍሪካ በባህር ኃይል የነበራትን ስም ዳግም ከፍ አድርገን እናስጠራለን ሲሉ ነው የገለጹት።