ቀጥታ፡

ለዘላቂ ሰላም መስፈን ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ጥናትን መሰረት በባደረገ መልኩ ለመፍታት እየተሰራ ነው- ሚኒስትር ብናልፍ አንዷለም

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ጥናትን መሰረት ባደረገ መልኩ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዷለም ገለጹ።

ሰላም ሚኒስቴር 'ኢንተርፒስ' ከተሰኘ ሲቪክ ድርጅት ጋር በመተባበር በሲዳማ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልሎች ያስጠናውን የሰላም ሁኔታ አመላካች ዳሰሳ ጥናት ሰነድ ዛሬ ይፋ አድርጓል።

የ'ፒስ ኢንዴክስ' ጥናት ሰነዱ በኢትዮጵያ አሁናዊ ሰላም ሁኔታ፣ የዘላቂ ሰላም ግንባታ ተግዳሮቶችና ዕድሎች እንዲሁም ለሰላም መረጋገጥ ድርሻ ያላቸውን ባለድርሻ አካላት ዝርዝር ሚናዎች ላይ አጠንጥኗል።
 

በጥናቱ ሂደት በሶስቱም ክልሎች የሚገኙ 808 ዜጎች፣ 101 ቀበሌ ሊቀ-መንበሮች እና 101 ባህላዊ መሪዎች መሳተፋቸውን ተገልጿል።

የሰላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና ሕዝባዊ አብሮነትን ለማጎልበት በርካታ ስራዎች ቢከናወኑም አሁንም ሰፊ የቤት ስራዎች እንዳሉ ጠቁመዋል።

የአገር ቀጣይነት ዋስትና ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ገልፀው፤ መንግስት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለዘላቂ ሰላም ለማስፈን በተቋማት ግንባታ እና ስርዓት መዘርጋት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በየጊዜው በሚያጋጥሟቸው ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ሳይበገሩ ዘመናት የተሻገረ ነባር የመረዳዳትና አብሮነት እሴቶች ማጎልበት ዘላቂ ሰላም ሁነኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል።
 

ሚኒስቴሩ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በመላ ሀገሪቷ ለሰላም መደፍረስ መንስኤ የሆኑ ችግሮችና መፍትሔዎችን በጥናት ለመለየት ስራዎች መጀመሩን ገልጸው፤ ጥናቱም የዚሁ ስራ አካል መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ከሶስት ዓመት በፊት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ቢታቀድም ባጋጠሙ አገራዊ ችግሮች ሳቢያ በሶስቱ ክልሎች ላይ እንደተወሰነና በቀጣይ በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ጥናቱ ማህበረሰቡን በቀጥታ ያሳተፈ እና በማህበራዊ አብሮነት ላይ ማተኮሩን የገለጹት አቶ ብናልፍ ጥናቱ የእስካሁን ተቋማዊ ጥረቶችን ለመፈተሽና የአጋር አካላትን ቅንጅታዊ አሰራር ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
 

የ'ኢንተርፒስ' ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳይመን ጊምሰን በበኩላቸው የዳሰሳ ጥናቱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሁሉን አቀፍ ጥረቶችን ውጤታማ ለማድረግ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ጥናቱ ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው የታችኛው ሕብረተሰብ ክፍል ጀምሮ በየደረጃው ባሉ ህብረተሰብ ክፍሎችን በመረጃ ግብዓትነት መጠቀሙን አንስተዋል።

የዘላቂ ሰላም ግንባታ ተግዳሮትና መፍትሔዎችን የዳሰሳ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ሚና እና ዘላቂ ሰላም አመላካች ጠቋሚዎችን ያሟላ ሰነድ ነው ብለዋል።

ከጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል "አብኮን" የተሰኘው ተግል ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሙሉ ተካ የማህበረሰቡ የሰላም አረዳድ፣ የማህበረሰቡ የግጭት አፈታት ልምድና አሳታፊነት እንዲሁም ሰላማዊነት፣ ግጭት፣ ምግብ ዋስትና፣ አዕምራዊ ደህነንት፣ ስርዓት ጾታ እኩልነት እና ጾታዊ እኩልነት ጥናቱ በጥልቀት የዳሰሳቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።

ሰላማዊ የግጭት አፈታት ዘዴ አለመጎልበት፣ ሴቶችና እና ወጣቶችን ውሳኔ ሰጨነት ማነስ እንዲሁም በአንዳንድ አካላት ብሔር ተኮር አስተሳስብ መጎልበቱ ለሰላም ግንባታ ተግዳሮት እንደሆኑ ነው የተገለጸው።

በዚህም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን የሰላማዊ ማህበረሰብ እና የማህበረሰብ አደረጃጀቶች ግንኙነቶች ወሳኝ ድርሻ እንዳላችው ጥናቱ አመላክቷል።
 

በማህበረሰቡ ዘንድ ግጭቶችን በማስቆም መቻቻል እና ማህበረሰብ አቀፍ ሰላም ለማስፈን የአካባቢ መሪዎች ውሳኔ ሰጭነት ትክክለኛነትና ሚዛናዊነት፣ የአገር ሽማገሌዎችና የቀበሌ አስተዳድሮች የእርስ በርስ ትስስርና ትብብር ማጠናከር ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተጠቁሟል።

ለማህበራዊ ትስስር መላላት መንስኤ የሆኑ የምግብ ዋስትና፣ አዕምራዊ ጤና፣ ስርዓተ ጾታ እኩልነት ችግሮችን ለመቅረፍ የፖሊሲ ጣልቃ ገብነት እና የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረት ይሻል ተብሏል።

በየክልሎቹ የማህበረሰቡ ተወካዮችን የእርስ በእርስ ግንኝነት ማጠናከር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በሕዝቡ ተሳትፎ መቅረፍ እንደሚገባ ተመላክቷል።

ሰነዱ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ እና ማህበረሰባዊ ውህደት ለማጎልበት የመንግስትና የሌሎች የባለድርሻ አካላትን ዘርፈ ብዙ አካሄድ፣ የማህበራዊ ወረቶች ሚና፣ አካታችነት፣ መረጃን መሰረት ያደረገ አገራዊ የሰላምና እርቅ ሂደቶች፣ የበይነ መንግስታትን ሚና ማጎልበት ዙሪያ ዝርዝር ምክረ ሃሳቦችን አካቶ መታተሙ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም