የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በ37 ማረሚያ ቤቶች ያደረገውን የታራሚዎች አያያዝ የክትትል ሪፖርት ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በ37 ማረሚያ ቤቶች ያደረገውን የታራሚዎች አያያዝ የክትትል ሪፖርት ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል በተመረጡ 37 ማረሚያ ቤቶች ያደረገውን የታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ የክትትል ሪፖርት ይፋ አደረገ።
ኮሚሽኑ በማረሚያ ቤቶች የሚገኙ የሕግ ታራሚዎችን አያያዝ በተመለከተ ባካሄደው የክትትል ሥራ ግኝቶችን ይፋ በማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቶ ምክረ-ሃሳቦችን አመላክቷል።
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተመረጡ 37 ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን የሰብአዊ መብት አያያዝ በአካል ምልከታ፣ የተለያዩ ሰነዶችን በማየት፣ ከታራሚዎችና ከማረሚያ ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በተደረጉ ቃለ-መጠይቆች መረጃውን ማደራጀቱ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጅማ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በዳሳ ለሜሳ፤ በተመረጡ ማረሚያ ቤቶች በተደረገው ክትትል በተለይም የታራሚዎች ሰብአዊ መብት አያያዝ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መቀበል፣ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴና ለመዝናኛ ማረሚያ ቤቶቹ የሰጡት ትኩረት መልካም መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም ማረሚያ ቤቶች ለቀለም ትምህርት የተሰጠው ትኩረትም መልካም መሆኑን ገልፀዋል።
በሕግ ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት ከማረሚያ ቤቶቹ ጋር ያላቸው ትስስር አነስተኛ መሆንና በአንዳንድ በማረሚያ ቤቶች ላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች መስተዋሉንም አረጋግጠናል ብለዋል።
ለአብነትም የማረሚያ ቤቱን ዓላማ፣ መተዳደሪያ ህግ እና ደንብ በማሳወቅ ረገድ ክትትል በተደረገባቸው ሁሉም ማረሚያ ቤቶች ውስንነት መኖሩን አንስተዋል።
በአንዳንድ ማረሚያ ቤቶች የታራሚዎችን በፍርድ መጠን፣ በእድሜ፣በጤና ሁኔታ፣ በወንጀል ታሪክ እና ህግ ጥበቃ ስር የዋሉበትን ምክንያት መሰረት አድርጎ መረጃ ያለመያዝና በዲጅታል ስርዓት አለማዘመንን ጠቅሰዋል።
የምግብ አቅርቦት፣የመጸዳጃ ቤቶች እና የመኝታ ቦታዎች ንጽህና ችግር፣ የንጹህ ውሀ አቅርቦት እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ዝውውር መቋረጡ አንዳንድ ማረሚያ ቤቶች ላይ መስተዋሉም አመላክተዋል።
በመሆኑም የሕግ ታራሚዎች መደበኛ ሰዎች የሚያገኙትን መብት የማግኘት መብት ያላቸው በመሆኑ ከጤና እና የትምህርት ቢሮዎች ጋር በቅንጅት መሰራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽነር ኢብራሒም ሐጂ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለይም በሰብአዊ መብት አያያዝ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል አለ ብለዋል።
በጤና አገልግሎትና በትምህርት ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ታራሚዎች የማረሚያ ቤት ቆይታ የሚታነጹበትና የሙያ ክህሎት የሚያገኙበት እንዲሆን ትምህርትና ሥልጠና እየተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባቀረበው ምክረ-ሃሳብ መሠረት ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ክፍተቶችን ለማስተካከል እንሰራለን ሲሉም ኮሚሽነሩ አረጋግጠዋል።
በጨፌ ኦሮሚያ የአስተዳደር፣ የሕግና የሰው ኃብት ልማት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገብሬ ኡርጌሶ፤ ከሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦችን በመቀበል ማረሚያ ቤቶች ሥራቸውን በተሻለ መልኩ መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
በተቋማት የሚፈቱ ጉዳዮች በተቋማት እንዲሁም በክላስተር መፈታት ያለባቸው ደግሞ በየደረጃው መፍትሔ እንዲያገኙ ይደረጋልም ነው ያሉት።
የሕግ ክፍተት የሚስተዋልባቸውን አሠራሮች በመለየት የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎች ቀጣይነት ያለው ውጤት እንዲኖራቸው ይሰራልም ብለዋል።