ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን በትግራይ ክልል የመሰረተ ልማቶች መልሶ ግንባታ የድርሻውን እንደሚወጣ ገለጸ

መቀሌ ሰኔ  20 /2015 (ኢዜአ)- በትግራይ ክልል በነበረው ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን  መሰረተ ልማቶች መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የድርሻውን እንደሚወጣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን  አስታወቀ።

በትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ለሚገኙ የምህንድስና ባለሙያዎች፣ ለህንፃ ተቋራጮችና አማካሪዎች ለሰባት ቀናት የሚቆይ የቴክኒክና ሙያ ተግባር ተኮር ስልጠና ከትላንት ጀምሮ በመቀሌ እየተሰጠ ነው።

የአቅም ግንባታ ስልጠናው በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢኒስቲትዩትና በትግራይ ክልል ግዜያዊ  አስተዳደር ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ  በትብብር መዘጋጀቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መስፍን ነገዎ እንዳሉት ባለስልጣኑ በትግራይ ክልል በጦርነት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት የድርሻውን ይወጣል።

ባለስልጣኑ በኮንስትራክሽን ዙሪያ ለተሰማሩ ባለሙያዎች ዘመኑ የሚጠይቀውን የቴክኒክና የሙያ ተግባር ተኮር ስልጠና መስጠቱ የእዚሁ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለመልሶ ግንባታው ስኬታማነት የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ታምራት ሙሉ "ፕሮጀክቶችን በእውቀት በመምራት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን ወደ ነበሩበት ለመመለስ በቅንጅት ይሰራል” ብለዋል።

ለምህንድስና ባለሙያዎች፣ የህንፃ ተቋራጮችና አማካሪዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠናም የዚሁ አካል መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢኒስቲትዩቱ  በመጠናቀቅ ላይ ባለው በጀት ዓመት  በአገር አቀፍ ደረጃ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለተሰማሩ  ከ2 ሺህ 500 በላይ  ባለሙያዎች በቴክኒክና ሙያ ላይ ያተኮረ  ሰልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ገብረ ፃዲቅ ስልጠናውን በትብብር እየሰጡ ያሉት ተቋማት የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ሥራን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ኢንጅነር ሃብታሙ አማረ በሰጡት አስተያየት ከተግባር ተኮር ስልጠናው በቂ ክህሎት እንደሚያገኙ አመላክተዋል። 

በስልጠናው ከክልሉ የተውጣጡ 150 የምህንድስና ባለሙያዎች፣ የህንፃ ተቋራጮችና አማካሪዎች እየተሳተፉ ነው። 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም