ዳያስፖራው ልዩነቶች ሳይገድቡት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ልዩነቶች ሳይገድቡት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፦የዳያስፖራው ማህበረሰብ ልዩነቶች ሳይገድቡት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የተለያዩ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች ገለጹ።
ኢትዮጵያ በርካታ ፈተናዎች በገጠሟት ወቅት የዳያስፖራው ማህበረሰብ በመንግስት የቀረበለትን አገራዊ ጥሪ በመቀበል ፈጣን ምላሽ መስጠቱ አይዘነጋም።
በፈተና ወቅት የአገርን ገጽታ ለማጠልሸት ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን በማጋለጥና እውነታውን ለማሳወቅ የንቅናቄ መረሃ ግብሮችን በማዘጋጀት ዳያስፖራው ኃላፊነቱን መወጣቱንም እንዲሁ።
በተለይም የቀረበውን አገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ወደ አገር ቤት በመምጣት የገንዘብ፣ የዓይነትና ሌሎች መሰል ድጋፎችን በማበርከት ለአገርና ለወገን አለኝታነታቸውን በተግባር ያሳዩበት ወቅት ነበር።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ዋና ፀሐፊ ዶክተር ፍትህ ወልደሰንበት፣ ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ የሚያደርገው ተሳትፎ በሁኔታዎችና ወቅቶች ላይ ብቻ መመስረት እንደሌለበት ነው የሚያነሱት።
ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያለች፤ የዜጎቿን ድጋፍና እገዛ የምትሻ በመሆኗ በውጭ የሚኖሩ የዳያስፖራው ማህበረሰብ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል።
ዳያስፖራው የፖለቲካና ሌሎች እሳቤዎችን ወደ ጎን በመተው ለአገሩና ለህዝቡ ቅድሚያ መስጠት እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።
ይህንኑ በሚመለከት ማህበሩ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑም ዋና ጸሃፊው አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማህበር የቦርድ ሰብሰቢ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ አገር በፈለገችው በማንኛውም ሁኔታ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በመሆን አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ ተሳትፎው በሁኔታዎችና ወቅቶች ላይ የተመሰረተ በመሆኑ በአገሩ ጉዳይ ላይ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ወጥነት የጎደለው እንዲሆን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በዳያስፖራው እየተደረገ ያለው የእውቀት፣የቴክኖሎጂና የፋይናንስ ድጋፍ የተበታተነ መሆኑም የተሻለ አበርክቶ እንዳይኖረው አድርጎታል ነው የሚሉት።
በመሆኑም መረጃን በተደራጀና አግባብነት ባለው መልኩ ተደራሽ በማድረግ የዳያስፖራውን ተሳትፎ የጎላ ለማድረግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በሰሜን አሜሪካ የጋምቤላ ዳያስፖራ ኮሙዩኒቲ መሪ ዲድሟ አጉዋለማ በበኩላቸው ኮሚዩኒቲው በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ በማድረግ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ተሳትፎን እንዲያጎለበት ከማስቻል አንፃር እየተደረገ ያለው ድጋፍ የተቀዛቀዘ መሆኑን አንስተዋል።
በመሆኑም መንግስት የዳያስፖራውን ማህበረሰብ የሚያሳትፉ የልማት ስራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ቀጣይነት ያለው የንቅናቄ ተግባራትን ማከናወን ይጠበቅበታል ብለዋል።
በዋናነትም ዳያስፖራው የማንንም ጉትጎታ ሳይጠብቅ ኢትዮጵያን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ ለሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይገባል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።