በ2014 በጀት ዓመት በ131 መስሪያ ቤቶች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ተገኝቷል- የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት - ኢዜአ አማርኛ
በ2014 በጀት ዓመት በ131 መስሪያ ቤቶች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ተገኝቷል- የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት
አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፦ በ2014 በጀት ዓመት በ131 መስሪያ ቤቶች ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በወቅቱ ያልተወራረደና ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ በኦዲት መረጋገጡን የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት አስታወቀ።
በበጀት ዓመቱ በገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች ያልተሰበሰበ ከ13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ተሰብሳቢ እዳ መኖሩንም አመልክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው 26ኛ መደበኛ ጉባኤው በ2014 በጀት ዓመት በፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ተወያይቷል፡፡
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበጀት ዓመቱ በፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የተከናወኑትን የፋይናንስ ሕጋዊነት ኦዲት እና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት አቅርበዋል።
በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተ ኦዲት በተደረጉ 131 መስሪያ ቤቶች በጠቅላላው ከ15 ቢሊዮን 125 ሚሊዮን ብር በላይ በወቅቱ ያልተወራረደና ያልተሰበሰበ ሂሳብ መኖሩ ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል።
የጤና ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በወቅቱ ያልተወራረደ ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ከተገኘባቸው ተቋማት ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ተሰብሳቢ ሂሳቦቹ ከዓመት ወደ ዓመት በሂሳብ መግለጫዎቹ ላይ የሚታዩ ከሆነ ተአማኒነትን ከማሳጣታቸውም በላይ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት ለብክነት ስለሚጋለጥ ተቋማቱ በደንብና መመሪያ መሰረት እንዲያወራርዱ እና መሰብሰብ የማይችሉትን ደግሞ አጣርተው እርምጃ እንዲወስዱ አስተያየት መሰጠቱን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች በደንብና መመሪያ መሰረት የመንግስት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ እዳ በ11 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና በ10 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች የግብር እዳ በድምሩ ከ13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ከ1 ዓመት እስከ 6 ዓመት ያስቆጠረ ውዝፍ ተሰብሳቢ እዳ መኖሩን የኦዲት ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ውዝፍ ገቢውን ካልሰበሰቡ መስሪያ ቤቶች መካከል በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ በጉምሩክ ኮሚሽን የቃሊቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የምዕራብ አዲስ አበባ ገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እና አዲስ አበባ መካከለኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሚጠቀሱ መሆናቸውንና በድምሩ ከ11 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ ገቢ እንዳለባቸው ተጠቅሷል፡፡
ገቢ መንግስት የሚያከናውናቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ለማስፋፋት ወሳኝ በመሆኑ የገቢ አሰባሰቡ ትኩረት እንዲሰጠውና ያልተሰበሰበው ውዝፍ ገቢ እንዲሰበሰብ በሪፖርታችን አሳስበናል ሲሉ ነው የፌደራል ዋና ኦዲተሯ ያመለከቱት።
በ2014 በጀት ዓመት የኦዲት ውጤት መሰረት ነቀፌታ የሌለበት 73፣ ከጥቂት ጉድለቶች በስተቀር አጥጋቢ ሆነው የተገኙ 66፣ አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው 6 እና የጎላ ችግር ያለባቸው ሆኖ በመገኘታቸው ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው ደግሞ 19 ተቋማት መሆናቸው በሪፖርቱ ላይ ተገልጿል፡፡
በበጀት ዓመቱ የተስተዋሉት የኦዲት ግኝቶች የጥሬ ገንዘብ እና የባንክ ሂሳብ አያያዝ፣ ውዝፍ ሂሳቦችን በወቅቱ አለመሰብሰብ እና አለማወራረድ፣ ተከፋይ ሂሳቦች፣ አለ አግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች፣ የገቢ ግብርና ታክስ አዋጅን አለመከተል፣ ደንብና መመሪያ ያልጠበቁ ግዢዎች፣ የውስጥ ገቢ አሰባሰብና አጠቃቀም፣የበጀት አስተዳደር፣በንብረት አጠቃቀም እና አስተዳደር የታዩ ጉድለቶች ዋናዎቹ መሆናቸውን ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ ያብራሩት።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተደረጉ ክዋኔ ኦዲቶች በርካታ የአሰራር ስርዓቶች በየመስሪያ ቤቶቹ ተዘርግተው አለመተግበራቸው ከተገኙ ግድፈቶች መካከል እንደሚጠቀስ አመልክተዋል።
የታዩትን የአሰራር ጉድለቶችና ክፍተቶች ለማረምና ለማስተካከል የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦችም በኦዲት ሪፖርቶቹ መካተታቸውን ጠቅሰዋል።
አስተያየት ሊሰጥባቸው ያልቻለ የፋይናንስ እና ሕጋዊነት ኦዲት ሪፖርቶች እንዲሁም ተቀባይነት የሚያሳጣ አስተያየት የተሰጠባቸው ተቋማት ኦዲት ሪፖርት አንድ ላይ ተደራጅተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ መላካቸውን ጠቁመው በሚመለከተው አካል ተመርምረው ተገቢ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሪፖርቱን አስመልክቶ የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን አንስተዋል።