ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማይደራደርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት ተገንብቷል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማይደራደርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የመጀመሪያ ዙር መሠረታዊ ባህረኞችን አስመርቋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ከአፍሪካ ቀዳሚና ጠንካራ የባህር ኃይል ከነበራቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗን ገልጸዋል።

በውስጥ ችግር ምክንያት ገናና የነበረው የኢትዮጵያ የባህር ኃይል ፈርሶ ለ30 ዓመታት መቆየቱን ጠቅሰው ኢትዮጵያ የባህር ኃይሏን አጥታ ቆይታለች ብለዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የ120 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ ታላቅ የሆነችውን ኢትዮጵያ ታላቅነቷን በሚመጥን መልኩ የባህር ኃይል መገባቱን ገልጸዋል።

የባህር ኃይሉ በማደግ ላይ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ቢሾፍቱ፣ ባህርዳር፣ ደብረብርሃን ላይ ትላልቅ መሠረተ ልማት እየተገነባለት መሆኑንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በርካታ ብቁ የሰው ኃይል በሀገር ውስጥና በውጭ እየሰለጠነ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በባህር ኃይል፣ በምድር ኃይል፣ በአየር ኃይል፣ በልዩ ኃይል እና የህዋ ኃይል ኢትዮጵያን የሚመጥን ጠንካራ ወታደራዊ ተቋም እየተገነባ ይገኛል ብለዋል ፊልድ ማርሻሉ።

በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የማይደራደርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚታገዝ አስተማማኝ የመከላከያ ሰራዊት መገንባቱንም አረጋግጠዋል።

በየትኛውም ፕሮፓጋንዳ የማይናወጥ በዲሲፕሊን የሚመራ፣ ከራስ በፊት ለሀገርና ለህዝብ የቆመ ጠንካራ ሰራዊት በመገንባቱን ጠቅሰው ለኢትዮጵያ ክብርና ሉአላዊነት ዘብ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም