ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መሠረት ያደረገ ነው- የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር 

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መሠረት  ባደረገ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ ገለጹ።

ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በዛሬው እለት በጃን ሜዳ አካባቢ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።

የአረንጓዴ አሻራቸውን ካኖሩት መካከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ፤ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ዘርፈ-ብዙ ዓላማዎችን አንግቧል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥና ቀጣናዊ ትስስርን የማሳለጥ ዕቅድ ያለው መሆኑን ገልፀዋል። 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋምና በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲሁም ለመኖሪያ ምቹ የሆኑ አካባቢዎችን ለመፍጠር ትልቅ ትርጉም ያለው መርሃ-ግብር መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም በአረንጓዴ አሻራ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በአረንጓዴ አሻራ ልማቱ ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብ ማጽደቅና ለሚፈለገው ዓላማ ስኬት መሥራትም ይገባል ነው ያሉት።
 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር አስቴር ዳዊት በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማት የህልውና መሠረት በመሆኑ የጋራ ጥረትና ትብብራችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
 

የኢትዮጵያ ባሕርና ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ድርጅት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲራጅ አብዱላሂ፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለተሻለ ስኬት በጋራ መሥራት አለብን ብለዋል።

ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ''ነገን ዛሬ እንትከል'' በሚል መሪ ሃሳብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአፋር ክልል በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

በዘንድሮው ክረምት ብቻ በአገር አቀፍ ደረጃ 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅድ መያዙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም