ቀጥታ፡

አውደ-ርዕዩ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለትውልድ የሚሻገሩ የምርምር ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን አሳይቷል - ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል     

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015 (ኢዜአ) አገር አቀፉ የጤና አውደ-ርዕይ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለትውልድ የሚሻገሩ የምርምር ሥራዎች እያከናወነች መሆኑን ያሳየ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል ገለጹ።  

የጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የጤና ክብካቤ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን በሳይንስ ሙዚየም ያዘጋጀው አገር አቀፍ የጤና አውደ-ርዕይ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተከፍቶ ለዕይታ ክፍት መሆኑ ይታወቃል፡፡

" የመጪው ትውልድ ጤና " በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው አውደ-ርዕይ የመንግሥትና የግል የጤና ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና በዘርፉ የምርምር ሥራዎችን ያከናወኑ ድርጅቶች ምርትና አገልግሎታቸውን ለዕይታ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና የቤተክርስቲያኗ አባቶች በሳይንስ ሙዚየም የተሰናዳውን አውደ-ርዕይ ጎብኝተዋል።



ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ በጉብኝቱ ወቅት በሰጡት አስተያየት አውደ-ርዕዩ ከአገር በቀል የሕክምና ዘዴዎች ጀምሮ ዓለም አሁን እስከደረሰበት ዘመናዊ የሕክምና ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ ቀርበዋል፡፡

የነገ አገር ተረካቢ ህፃናት ስለ ሕክምና የበለጠ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ትዕይንቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡

የቀረቡት ሀገር በቀል የሕክምና ዘዴዎችም ኢትዮጵያ በራሷ አቅም የዘርፉን ችግሮች እንድትፈታ የሚያስችሉ መንገዶችን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

የሕክምና እውቀት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የሚሄድ መሆኑን ገልጸው፤ አውደ-ርዕዩ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገሩ ሥራዎች እየተሰሩ ለመሆናቸው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ቤተክርስቲያኗ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በመላ አገሪቱ ባሏት የሕክምና ተቋማት በጤናው ዘርፍ አገልግሎት እየሰጠች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡

በካቶሊካዊት ዩኒቨርሲቲ በኩልም የሕክምና ትምህርት ክፍል በመክፈት የጤና ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሰራች መሆኗንም ጠቁመዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም