ቀጥታ፡

ከየትኛውም የውሃ አካል ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት በብቃት የሚመክት ባህር ኃይል እየተገነባ ነው- የባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2015(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብርና ከየትኛውም የውሃ አካል ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት በብቃት የሚመክት ባህር ኃይል እየተገነባ መሆኑን የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን የመጀመሪያ ዙር መሠረታዊ ባህረኞች አስመርቋል።

የኢትዮጵያ ባህር ኃይል ዋና አዛዥ ሪር አድሚራል ክንዱ ገዙ፤ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ዘመናዊ የባህር ኃይል ያቋቋመችው በ1948 ዓ.ም እንደነበር አስታውሰዋል።

የባህር ኃይሉ ለ30 ዓመታት ህልውናው ጠፍቶ እንደነበርና ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአፍሪካ ገናና ስም የነበረውን የባህር ኃይል ትንሳኤ ዳግም ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድ አለመረጋጋት ያለበት የበርካታ ሀገራት የጦር ሰፈር የገነቡበት፣ የተደራጁ የውሃ ላይ ዘራፊዎች ያሉበት መሆኑን በማንሳት ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የባህር ኃይልን ዳግም ማቋቋም የግድ ብሏታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ ወጪና ንግድ መመላለሻ ኮሪደሯ በጂቡቲ በኩል ከመሆኑና በቀጣናው ካለው ሽኩቻ አንፃር የባህር ኃይሏን በ2011 ዓ.ም መልሳ ማቋቋሟን ገልጸዋል።

ከሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ አውድ አኳያ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የባህር ኃይሏን በጠንካራ አደረጃጀት እየገነባች መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ለዚህም በመሠረታዊ ባህረኝነት፣ በማሪን ኮማንዶና ሌሎችም ሥራዎች የተለያዩ የሰው ኃይል ግንባታ ሥራዎችና በተቋማት አደረጃጀትና ሌሎችም መስኮች የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከየትኛውም የውሃ አካላት ሊሰነዘር የሚችልን ጥቃት በብቃት መመከት የሚያስል የባህር ኃይል እየተገነባ ነው ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም