በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ
ሐረር፤ ሰኔ 20 /2015 (ኢዜአ)፡ - የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን የሐረር ቅርንጫፍ በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሁለት ወረዳዎች ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቻቸው የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ፡፡
ፕሮጀክቶቹን በቤተ ክርስቲያኒቱ የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አንጀሎ፣የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ አበበ፣የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የገጠር መጠጥ ውሃ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ብርሃኑ ወንዳፍራውና የዞኑ አመረራሮች መርቀዋል።
በቤተ ክርስቲያኗ የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን የሐረር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፕሮጀክት አስተባባሪ ዶክተር በላይ አለማየሁ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በዞኑ ጎሮጉቱ እና ባቢሌ ወረዳዎች የተገነቡት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከ17 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ መስመር የተዘረጋላቸው ናቸው።
በታቀደላቸው ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁት የውሃ ፕሮጀክቶች 28 የውሃ ማደያዎችና እስከ 75 ሺህ ሜትር ኪዩብ መያዝ የሚችሉ የውሃ ማጠራቀሚያዎች እንዳሏቸው አስታውቀዋል።
ከ12ሺህ በላይ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
ለውሃ ፕሮጀክቶቹ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና በፀሐይ ሀይል የሚሰራ ማመንጫ ግንባታ እንደተከናወነላቸውም ዶክተር በላይ ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር የገጠር ውሃ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ብርሃኑ ወንዳፍራው በበኩላቸው፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ የገጠሩ ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ሚኒስቴሩ በርካታ ስራዎችን በማከናን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በቤተ ክርስቲያኗ የተገነቡት ፕሮጀክቶች የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በማሳደጉ ረገድ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ አበበ፤ በፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሂደት ህብረተሰቡ ላበረከተው የጉልበት አስተዋጽኦ ምስጋና በማቅረብ ተንከባክቦ መጠበቅ እንዳለበትም አመልክተዋል።
ድርጅቱ የጀመረውን የልማት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን የውሃና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጀማል ሐሰን በበኩላቸው ፥የገጠሩን ማህበረሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን ላደረገው ድጋፍ ምሰጋና አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ በአስቸጋሪ መልከዓ ምድር መገንባቱ፣ በታቀደው ጊዜና በጀት መጠናቀቁ ለሌሎች ቀጣይ ሥራዎች ልምድ የተገኘበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በጎሮ ጉቱ ወረዳ የመካኒሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መካ ኢብሮ በሰጡት አስተያየት፤ በቀበሌው ለዓመታት ሲያቀርቡት ለነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ጥያቄ አሁን ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
" ለስምንት ሰዓታት ከኩሬና ከወራጅ ወንዝ ውሃ ፍለጋ መንከራተት ቀርቶልናል ፤ ችግራችን ተፈቶልናል፤ የሰራልንንም አካል እናመሰግናለን" ብለዋል፡፡
በአካባቢያቸው የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር መፍትሄ በማግኘቱ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ በባቢሌ ወረዳ የራህመታ ሰላማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ነኢማ መሀመድ ናቸው።
"አሁን ላይ ችግሩ መፈታቱ ለኛም፣ ለልጆቻችንም ለሁሉም ማህበረሰብ ትልቅ እፎይታ ነው" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የማህበራዊና ልማት ኮሚሽን የሐረር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በምስራቅ ሐረርጌ ዞን አራት ወረዳዎች በቅርቡ ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመስኖ ፕሮጀክቶችን አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱም ተገልጿል።