ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር ሰላሙን በማጽናትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል- ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ - ኢዜአ አማርኛ
ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር ሰላሙን በማጽናትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል- ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015 (ኢዜአ) ህዝበ ሙስሊሙ የአረፋ በዓልን ሲያከብር ሰላሙን በማጽናት በአንድነት፣ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ገለጹ።
የጠቅላይ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ፤ ለ1 ሺህ 444ኛ ዓመተ ሂጂራ የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሳኡዲ አረቢያ የሃጂ ስነ-ስረዓት ላይ የሚገኙት ፕሬዝዳንቱ በዘንድሮው የሐጂ ጉዞ ከኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሁጃጆች የተሳተፉበት መሆኑን ገልጸዋል።
የአረፋ በዓልን ህዝበ ሙስሊሙ ሰላሙን በማጽናት በአንድነት፣ በመረዳዳትና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ ሸህ ሀሚድ ሙሳ በበኩላቸው፤ የአረፋ በዓል በእምነቱ ዘንድ ጥልቅና ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን አብራርተዋል።
በማብራሪያቸውም ዕለቱ ከሰማይ ወደ መሬት የወረዱት አደምና ሐዋ ከመጠፋፋት በኋላ በሳዑዲ አረቢያ አረፋ ተራራ የተገናኙበትን ክስተት እና ከረመዳን ጾም ቆጥሎ የሚፈጸም ኢስላማዊ ስርዓት ነው ብለዋል።
ሐጂ ማለት ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ሁጃጆች ያለምንም ልዩነት ዱዓ እያደረጉ የአደም ልጅነታቸውን ብቻ የሚያስምሰክሩበት የመዳን ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።
የአረፋ በዓል ሲከበር አቅም የፈቀደለት ሁሉ ዕርድ ፈፅሞ በአብሮነት፣ በፍቅር፣ በመረዳደትና ተካፍሎ በመብላት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከበር ይሆናል።