በበጀት ዓመቱ 10 ወራት አገራችን 2 ነጥብ 94 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች--የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ 10 ወራት አገራችን 2 ነጥብ 94 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች--የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ
ሀዋሳ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ)፦በበጀት ዓመቱ አስር ወራት ኢትዮጵያ 2ነጥብ 94 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሏን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ገለጹ።
በኢንቨስት ኢትዮጵያ ንቅናቄ ወቅትም ወደ ሃገራችን ከገቡት ከ1 ሺህ 200 ከሚበልጡ ባለሃብቶች ጋር የ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ስምምነት መፈረሙን ተናግረዋል።
የኮሚሽኑንና የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የሌሎች ባለድርሻ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች ዛሬ የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን የሥራ እንቅስቃሴ በመመልከት ከባለሀብቶች ጋር ተወያይተዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ከውይይቱ በኋላ በተለይም ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በበጀት አመቱ አስር ወራት የ2 ቢሊዮን 940 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የኢንቨስትመንት ፍላጎት መሳብ ችላለች።
"ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ9 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ብልጫ አለው" ብለዋል።
ፍላጎቱን ያሳዩ የውጪ ባለሀብቶች በዋናነት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆናቸውን ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
የውጪ ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ለማድረግ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ኮሚሽነሯ በተለይም ባለፈው ሚያዝያ በነበረው የኢንቨስት ኢትዮጵያ ንቅናቄ ከ1 ሺህ 200 በላይ የውጪ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ያለውን አቅም እንዲያዩ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ከባለሀብቶቹ ጋር በተደረሰ ስምምነትም ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ስምምነት መፈረሙን ጠቁመው "ይህን ወደ ስራ መለወጥ ሁላችንም ሀላፊነት አለብን" ብለዋል።
በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ባደረጉት ጉብኝትም በፓርኩ ያሉ ባለሀብቶች እየሰሩ ያሉበትን ሁኔታ ከማየት ባለፈ በተደረገ ውይይትም ያሉባቸውን ችግሮች መረዳት እንደተቻለ አመልክተዋል።
በፓርኩ እየሰሩ ካሉ ባለሀብቶች አንዳንዶቹ ያላቸውን ቦታ በአግባቡ በመጠቀም ተጨማሪ የማስፋፊያ ስፍራ መጠየቃቸውንም ጠቁመዋል።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም በሰው ሀይል ቅጥር፣ በወጭ ንግድና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች እድገት እያሳየ መሆኑን መገንዘባቸውን ኮሚሽነሯ አስታውቀዋል።
“በውይይቱ ከገንዘብ ሚንስቴር፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከንግድ ባንክና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት እንደተገኙ ገልጸው የተነሱ ችግሮች አንዳንዱ ከባለሀብቱ ጋር በቅርበት መስራት የሚጠይቁና አንዳንዶቹ ደግሞ ወስደን ማስተካከልና ማረም የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ አይተናል” ብለዋል።
ኮሚሽነሯ አክለው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክም በሰው ሀይል ቅጥር፣ በወጭ ንግድና በሌሎች የስራ እንቅሰቃሴው እያደገ መምጣቱን መመልከታቸውን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው በሀገራችን ከተደረገው የሰላም ስምምነት በኋላ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴው ሳቢና አትራፊ እንዲሆን ለማድረግ መንግስት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በጉብኝቱና ከባለሀብቶች ጋር በተደረገው ውይይት በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮች የተገኙበት መሆኑን ዋና ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
"ከባለሀብቶች እንደ ችግር የተነሱ ጉዳዮችን ለመፍታት እንደ የቤት ስራ የያዝናቸው እንዲሁም ከባለሀብቱ አንጻር መወጣት ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አመላክተን ተግባብተናል" ብለዋል።
በአጠቃላይ የነበረው ውይይት ገንቢ እንደነበር ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።