ቀጥታ፡

የአረፋ በዓልን  የተቸሩ ወገኖችን በመደገፍና ማዕድ በማጋራት እናከብራለን - የእምነቱ ተከታዮች 

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015 ( ኢዜአ)፦  የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓልን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ እና ማዕድ በማጋራት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች ገለጹ።

1444ኛው የኢድ አል አድሃ  ከነገ በስቲያ በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።

የአረፋ በዓል ሲከበር የእርድ ሥነ-ሥርዓት የሚከናወን በመሆኑ የተለያዩ እንስሳት ለመስዋዕትነት ይቀርባሉ።

ከእርዱም ማንኛውም ሙስሊም አንድ-ሦስተኛውን ለድሃ፣ አንድ-ሦስተኛውን ለጎረቤትና ቤተ-ዘመድ እንዲሁም አንድ-ሦስተኛውን ለቤተሰቡ በመከፋፈል በዓሉን የሚያሳልፍ ይሆናል።


 

ከዚሁ የበዓል አከባበር ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች ሃይማኖቱ በሚያዘው መሰረት አረፋን ለማክበር ዝግጅት አድርገናል ብለዋል። 

በመሆኑም የዘንድሮውን የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ስናከብር በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን በመደገፍና ማእድ በማጋራት ይሆናል ብለዋል።

ካነጋገርናቸው መካከል ሸህ ሻፊ ሸሪፍ እና ሸህ መሃመድ አሚን፤ የአረፋ በዓልን እምነቱ በሚያዘው መሰረት ለማክበር ተዘጋጅተናል ሲሉ ገልጸዋል።

የአረፋ በአል የሚከበረው ያለው እርድ በመፈፀም ዘመድ አዝማድ፣ ጎረቤት በመጠየቅና ለተቸገሩ ወገኖች በማካፈል በመሆኑ በዚሁ መሰረት ለማክበር ተዘጋጅተናል ነው ያሉት።

የኢድ አል አደሃ በዓል ሲከበር ቅራኔን በማስወገድ በአብሮነት፣ በመተጋገዝና በመረዳዳት በመሆኑ በዚሁ መሰረት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ሸህ ሻፊ ሸሪፍ እና ሸህ ፉአድ ፈድሉ ገልጸዋል።

ሸህ መሃመድ አሚን  እና ሸህ ሙሃመድ ዘይን፤ በመልእክታቸው ህዝበ ሙስሊሙ  የአረፋ በዓልን  ስያከብር የተቸገሩ ወገኖችን መደገፉ አንዳለ ሆኖ ለአገር ሰላምና አብሮነት አጽኖት በመስጠትም ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከበር ይሆናል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም