ቀጥታ፡

ቻይና በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን ለማሳደግ ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጸች

አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ) ቻይና በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ልማትን በማሳደግ የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ ካውንስለር ያንግ ይሀንግ ገለጹ።

የኢትዮጵያ፣ የቻይና መንግስት እና የተመድ የልማት ፕሮግራም የባዮ ጋዝ፣ የባዮማስ እና የፀሐይ ኃይል የደቡብ ደቡብ የሶስትዮሽ የልማት ትብብር ማዕቀፍን መሰረት ያደረገ አዲስ የፕሮጀክት ስምምነት ተፈራርመዋል።


 

በሶስትዮሽ የትብብር ስምምነቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፣ የቻይና መንግስት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ተወካዮች ተገኝተዋል። 

ዶክተር ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ፤ ከዚህ ቀደም በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በትብብር ለመስራት የሦስትዮሽ ስምምነት ተፈርሞ የነበረ ቢሆንም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ሳይተገበር ቆይቷል ብለዋል።



 

ስምምነቱ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲና አካባቢው፣ በሀረር ከተማ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በአማራ ክልል በባዮ ጋዝ፣ በፀሐይ ኃይል የታዳሽ ኃይል ልማት ለማካሄድ የሚያስችል እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ዛሬ የተፈረመው ስምምነት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በማካተት በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይልን በስፋት የማመንጨት አቅምን በመጨመር የዜጎችን የኃይል ፍላጎት ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።

በስምምነቱ መሰረት የታዳሽ ኃይል ማመንጫ ስራውን የሚያግዝ የምርምር ማዕከል ለማቋቋም እና የተመራማሪዎችን አቅም ለማጎልበት እንደሚሰራም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና የንግድ ካውንስለር ያንግ ይሀንግ፤ ቻይና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ከአፍሪካ ጋር በዘርፈ ብዙ የልማት መስኮች በትብብር እየሰራች ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም የታዳሽ ኃይል የምርምር ማዕከል ለማቋቋም እና የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን ለማስፋት የተደረሰው የሶስትዮሽ ስምምነት የዘርፉን እድገት ለመደገፍ መሰረት የሚጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን በማስፋት የዜጎችን ህይወት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ቻይና በጠንካራ የፖሊሲ እርምጃ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ ክሊዮፋስ ቶሮሪ፤ የታዳሽ ኃይል አማራጭ ልማትን ማስፋት የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።


 

የሶስትዮሽ የትብብር ስምምነቱም በባዮ ማስ፣ ባዮ ጋዝ እና በፀሐይ የታዳሽ የኃይል አማራጭ ልማትን ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከቻይና መንግስት ጋር በመተባበር በደቡብ ደቡብ የትብብር ማዕቀፍ መሰረት የዜጎችን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም