ኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ አቅርቦትን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት የልማት አጋሮች እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ አቅርቦትን ለማረጋገጥ እያደረገች ያለውን ጥረት የልማት አጋሮች እንዲደግፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የውሃና ኢነርጂ አቅርቦትን ለማረጋገጥ እያደረገች ላለው ጥረት የልማት አጋሮች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን /WASH/ በውሃ ልማት እና ኢነርጂ ላይ ትኩረቱን ያደረገውና ለሁለት ቀናት የሚቆየው 11ኛው ጉባኤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።
በዚህ ወቅት እንደተጠቀሰው ዜጎችን በንጹሕ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ ተደራሽነትን የማስፋት ተግባራት እየተከናወኑ ነው ተብሏል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ኢተፋ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት 62 በመቶ ላይ ይገኛል።
ይህን ከፍ ለማድረግ በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሁሉም ዜጋ በአቅራቢያው ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ አቅርቦትን ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር ጠንካራ የሆነ ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢነርጂ ዘርፉን ለማሳደግም በርካታ ስራዎች መስራታቸውን ገልጸው ግድቦችን ጨምሮ ሌሎች የኢነርጂ አማራጮችን ለማስፋት ትኩረት መደረጉን አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት ከ20 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የኃይል ማስተላለፊያ የመስመር ዝርጋታ መከናወኑን ተናግረው በዚህም በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የገጠሩን ማህበረሰብ የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ በታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ስኬታማ ስራዎች መከናወናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የጉባኤው ዋና ዓላማም ኢትዮጵያ በውሃ፣ በኢነርጂ እና በሳኒቴሽን ዘርፎች ያከናወነቻቸው መልካም ስራዎች ይበልጥ እንዲሰፉና አጋር አካላትም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ማስቻል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ስኬታማ የሚባል የአረንጓዴ አሻራ ተግባራትን ማከናወኗን ጠቁመው ይህም ዓለምን በመፈተን ላይ የሚገኘውን የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም የልማት አጋሮች ኢትዮጵያ እያከናወነች የምትገኘውን የአረንጓዴ አሻራ ስራ ማገዝ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ማህበረሰቡ በሳኒቴሽን እና ሃይጂን ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና የባህሪይ ለውጥ ለማምጣት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም በመላው ሀገሪቱ የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ-ግብር እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት(ዩ.ኤስ.ኤ.አይ.ዲ) ተጠባባቂ የሚስዮን ዳይሬክተር ቲሞቲ ስቴይን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 500 ሺህ ሰዎች መሰረታዊ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ 65 ሚሊዮን ዶላር መመደቡን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን /WASH/ ዘርፍም 350 ሺህ ሰዎችን ተጠቃሚ ለማድግ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
በጉባኤው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ የጤና ሚኒስቴር እና የገንዘብ ሚነስቴር ከፍተኛ አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ የልማት አጋር ተቋማት ኃላፊዎችን ጨምሮ የዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።