አብሮነት፣ ሰብአዊነትና አለኝታ በተግባር የሚገለጥበት ታላቅ በዓል - ዒድ አል-አድሃ (አረፋ)

በሰለሞን ተሰራ 

በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ በዓላት መካከል አንዱ የእርድ ወይም የመስዋዕት በዓል የሆነው ዒድ አል-አድሃ (አረፋ) ነው፡፡ 

ነብዩሏህ ኢብራሒም ከ120 ዓመታት የመካንነት ሕይወት በኋላ በአሏህ ፈቃድ ወንድ ልጅ ተቸራቸው፡፡ የተወለደው ልጃቸው ዒስማኢልም ለአባቱ ታዛዥ እንደነበር በቅዱስ ቁርዓን ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

በደስታቸው ማግስት የእምነታቸው ጽናት የሚፈተንበት ወቅት በመፈጠሩ የሰባት ዓመት አንድያ ልጃቸውን ለመስዋዕት እንዲያቀርቡ ነብዩሏህ ኢብራሒም በፈጣሪ ታዘዙ፡፡

የልጃቸው ፍቅር ቢያስጨንቃቸውም ትዕዛዙ የመጣው ከፈጣሪያቸው በመሆኑ የእምነታቸውን ግዳጅ ለመወጣት  ከመካ ወደ አረፋ ተራራ ወጡ፡፡

ነብዩሏህ ኢብራሒም ልጃቸውን ለመሰዋት በመዘጋጀት ላይ እያሉም በልጃቸው ምትክ ፈጣሪያቸው የመስዋዕት በግ በማዘጋጀት ያቀረበላቸው መሆኑን ተከትሎ በዓሉ ዒድ አል-አድሃ (አረፋ) እየተባለ በየዓመቱ ይከበራል፡፡

በኢትዮጵያ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች በአልባሳት ደምቀውና አምረው በተክቢራ ታጅበው/ፈጣሪን እያወደሱ/ በጀመዓ (በኅብረት) አንድ ቦታ ላይ ተሰባስበው ይሰግዳሉ።

ከሰላት መልስም የእርድ ሥነ-ሥርዓት (ኡዱሒያ) አከናውነው ከተቸገሩ ወገኖችና ከጎረቤቶች ጋር ጭምር በመካፈል በዓሉን ያከብራሉ።

የዐረፋ በዓል በእስልምና እምነት አምስቱ መሠረቶች አንዱ ከሆነው ከሐጅ ሥነ-ሥርዓት (የአሏህን ቤት ከመዘየር) ጋር የተያያዘ ሲሆን የሐጅና ዑምራ ሥርዓቶችም ይከናወኑበታል። 

በአረፋ ወቅት ከሚከናወኑት ሃይማኖታዊ ተግባራት ውስጥ ዋናዎቹ የሐጅ ሥርዓት ማከናወን (ካዕባን) መዘየርና መጠወፍ እንዲሁም ኡዱሒያ (ዕርድ) ማድረግ ናቸው፡፡ 

ኡዱሒያ (ዕርድ) የሚከናወንበት ምክንያት አሏህ ነብዩሏህ ኢብራሒምን ልጃቸው ዒስማኢልን እንዲሰዉ  ታዘው የአሏህን ትዕዛዝ ያለምንም ማመንታት ለመፈጸም ልጃቸውን ለእርድ ሲያዘጋጁ ጅብሪል (አለይህ ሰላም) በግ አምጥቶ እንዲቀይርላቸው ታዘዘ፡፡ 

በዚህም ምክንያት ነብዩሏህ ኢብራሒም በልጃቸው ዒስማኢል ፋንታ ከፈጣሪያቸው የቀረበላቸውን በግ በማረድ የአሏህን ትዕዛዝ በመቀበል ልጃቸውን ለመሰዋት በመዘጋጀት ታማኝነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል።

በዚህም ምክንያት የአረፋ በዓልና የእርድ ሥነ-ሥርዓት የተቆራኙ ሆነው በእለቱ ግመል፣ በሬ፣ በግ እና ፍየል የሚታረዱ ይሆናል።

አንድ ሰው ከሚያከናውነው እርድም አንድ-ሦስተኛው ለድሃ፣ አንድ-ሦስተኛው ከጎረቤትና ቤተ-ዘመድ እንዲሁም አንድ-ሦስተኛው ለቤተሰቡ በመከፋፈል በዓሉን እንዲያሳልፍ ሃይማኖታዊ አስተምህሮው ያዛል፡፡ 

የአረፋ በዓል የመተሳሰብና የመረዳዳት ሃይማኖታዊ እሴት ሲሆን የሰዎች አብሮነት፣ ሰብአዊነትና አለኝታ በተግባር የሚገለጥበት ታላቅ ሁነት መሆኑ ይነገራል።

የአረፋ በዓል በኢትዮጵያ በአብሮነትና በመረዳዳት የሚከበር ከመሆኑ ባለፈ በተለያዩ ምክንያቶች ተራርቀው የቆዩ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና ዘመድ አዝማዶች የሚገናኙበት ታላቅ በዓል ነው።

በአረፋ በዓል በአንዳንድ አካባቢዎች ተጫጭተው የቆዩ ወጣቶች የሚሞሸሩበት፣ ሌሎች ትዳር ለመመስረት የሚዘጋጁበትና በየአካባቢያቸው ባህልና እምነቱ በሚያዘው መሠረት የትዳር አጋር ምርጫ የሚያደርጉበት መሆኑ ይነገራል።

የአረፋ በዓል በተለያዩ ምክንያቶች ቅራኔ ውስጥ የነበሩ ሰዎችም ይቅር ተባብለው የሚዘያየሩበት/የሚጠያየቁበት/ የፍቅርና አብሮነት በዓል መሆኑን የእምነቱ አባቶች ያስረዳሉ። 

የእስልምና እምነት ኩርፊያንና ይቅር አለመባባልን አጥብቆ የሚከለክል ቢሆንም በምንም አጋጣሚ ይሁን የነበረ መቃቃርን በአረፋ ይቅር (አውፍ) በመባባል በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመጠያየቅ ማክበር ያስፈልጋል ይላሉ ኡለማዎች።

ከዚህ በኋላም ሰዎች የቤተሰብን ሕይወት እንዲሻሻል፣ የአገር ሰላም እንዲጸና እና አብሮነት እንዲጎለብት የሚመካከሩ ይሆናል።

የአረፋ በዓል አከባበር ከሃይማኖታዊ እሴቱም ባለፈ በርከት ያሉ ቤተሰባዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎች ያሉት በመሆኑ በተለየ መልኩና በድምቀት የሚከበር በዓል ነው።

የዐረፋ በዓል አከባበር በሌሎች  ሀገራት

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሀገራት እና ሙስሊሞች በዓሉን የሚያከብሩበት ሂደት ከባህል እና ከእሴት ልዩነት ጋር በተያያዘ የሚያከብሩበት አውድ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡

በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓልን ለማክበር ሦስት ተከታታይ ቀናትን ይጠቀማሉ፡፡ 

ከዒድ አል-አድሃ በዓል ቀድማ ያለችዋን ቀን በልዩ ሁኔታ ሲያከብሯት ስያሜዋንም “አረፋ” ይሏታል፡፡ ከዋዜማው ቀን ጀምረው “ዒድ ሙባረክ” በመባባል የደስታ መልዕክት ይለዋወጣሉ፡፡

ህፃናት በበዓል አልባሳት ደምቀው የዒድ ስጦታ ለጎረቤቶቻቸው በማበርከት ያሳልፋሉ፡፡ እናቶች መኖሪያ ቤቶቻቸውን በዒድ መልዕክቶች ያሳምራሉ፤ ተወዳጅ እና ጣፋጭ ምግቦች በተለየ ሁኔታ ለቤተሰቡ ይዘጋጃሉ፡፡

በቱርክ በመጀመሪያው የዒድ አል-አድሃ ቀን ወንዶች ለተለየ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ወደ መስጂድ በጠዋት ይሄዳሉ፡፡ 

ተርኪዬ/ቱርካውያን/ በዒድ አል-አድሃ ለበዓሉ በሚመጥን አልባሳት ደምቀው ቤተ-ዘመድ ይጎበኛሉ፤ ጥሪ አድርገው በቤታቸው ይጋብዛሉ፤ እንዲሁም የኃብት አቅም ለሌላቸው ወገኖች ድጋፍ ያደርጋሉ፤ አሁን አሁንም ለመስዋዕት የሚቀርበውን እንስሳ ለበጎ አድራጎት እያዋሉ ይገኛሉ። 

በመሆኑም 1 ሺህ 444ኛው የዒድ አል-አድሃ (አረፋ) በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች የሚከበር ይሆናል።

ዒድ ሙባረክ!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም