በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ‘ብሩህ ትውልድ’ የተሰኘ ፕሮጀክት አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ‘ብሩህ ትውልድ’ የተሰኘ ፕሮጀክት አስጀመሩ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ)፦ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ክህሎት ለማሳደግ የሚሰራው ‘ብሩህ ትውልድ’ የተሰኘ ፕሮጀክት በይፋ አስጀምረዋል።
ፕሮጀክቱ ከ10 እስከ 12 ሳምንት እንደሚቆይ ተገልጿል።
የ‘ብሩህ ትውልድ’ ፕሮጀክት ዓላማ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ፈጣሪዎች እና ችግር ፈቺ ዜጎች እንዲሆኑ ስልጠና መስጠት መሆኑን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታውቋል።
የፕሮጀክቱ ተባባሪ መስራች እና የአሜሪካው የጠፈር ድርጅት(ናሳ) ሳይንቲስት ዶክተር ብርሀኑ ቡልቻ ፕሮጀክቱ ቀጣይ ትውልዶችን በመቅረጽ የሕይወት ዘመን ተማሪዎች እና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማብቃት መሆኑን ገልጸዋል።
ሂደቱም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ምሁራን ዳያስፖራዎች እና ዓለም አቀፍ በጎ ፈቃደኞች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች በጥሩ ውጤታቸው የተመረጡ ተማሪዎችን የሚያስተምሩበት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ከ10 እስከ 12 ሳምንታት እንደሚቆይ የጠቀሱት ዶክተር ብርሃኑ በመላው ኢትዮጵያ ከሚገኙ 35 ማዕከላት የተውጣጡ 750 ተማሪዎችን ተቀብሎ ስራ መጀመሩን አመልክተዋል።