ቀጥታ፡

መርሃ ግብሩን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል- አፈ ጉባኤ  አቶ አገኘሁ ተሻገር 

ጅግጅጋ ሰኔ 19/2015 (ኢዜአ) የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት ይገባል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አስገነዘቡ።

አፈ ጉባኤው በሶማሌ ክልል ደረጃ የሚካሄደውን የሁለተኛ ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ዛሬ በጅግጅጋ ከተማ በሚገኘው ገርባሳ የፖሊስ ኮሌጅ ችግኝ በመትከል አስጀምረዋል ። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንዳሉት ከአራት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የአካባቢ መራቆትና ጉስቁልናን ለመከላከል የላቀ ጠቀሜታ እያበረከተ ነው። 

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ችግርን ለመፍታት አስተዋጾው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።

መርሃ ግብሩን በአግባቡ ተግባራዊ በማድረግ ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የአራንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በሚቀጥሉት አራት ዓመታት የፍራፍሬና የእንሰሳት መኖ ጨምሮ ከ25 ቢሊየን በላይ ችግኞች ለመትከል ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።


 

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢብራሂም ኡስማን በበኩላቸው በሶማሌ ክልል ባለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ ድርቅ መከሰቱን አስታውሰው ዋነኛ መካላከያ መንገዱ አካባቢን በደን መሸፈን መሆኑን አመልክተዋል። 

አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በድርቅና ጎርፍ አደጋ  ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ በክልሉ በሁሉም ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች  ለመርሃ ግብሩ ትግበራ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ አሳሰዋል። 

"አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  የደን ሽፋን ከማሳደጉ በተጨማሪ የተራቆተ መሬት ወደ ቀድሞ ስፍራው እንዲመለስ፣ የተጎዳ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሀ እንዲጎለብት አስችሏል" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም ናቸው።


 

የሶማሌ ክልል የአካባቢ ጥበቃና የገጠር መሬት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሙህየዲን አብዲ በበኩላቸው  በሶማሌ ክልል በመጀመሪያው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 26 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ 17 ሚሊዮን መተከሉን አስታውሰዋል። 

ያለፉት ዓመታት ተሞክሮን በማስፋት በሁለተኛው ምዕራፍ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመጀመሪያ ዙር 13 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል ።

"ነገን ዛሬ እንትከል" በሚል መርህ በሶማሌ ክልል ደረጃ ዛሬ በተጀመረው ሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት ላይ የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም