አዲስ የስንዴ መውቂያ ቴክኖሎጂ ለግል አምራቾች ሽግግር መደረጉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ የስንዴ መውቂያ ቴክኖሎጂ ለግል አምራቾች ሽግግር መደረጉን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ)፦ አዲስ የስንዴ መውቂያ ቴክኖሎጂ ለግል አምራቾች ሽግግር መደረጉን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
በግብርና ሚኒስቴር እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ተጠሪ ተቋማት ቅንጅት የተገኘውን ቴክኖሎጂ እንዲያባዙ ለግል አምራቾች ሽግግር መደረጉም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት እና የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የአዲሱ የስንዴ መውቂያ ቴክኖሎጂ አመንጪዎች መሆናቸውም ተጠቁሟል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ቴክኖሎጂን ማመንጨት ብቻውን በቂ ስላልሆነ ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ቴክኖሎጂውን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ለማድረግ ብድር ማመቻቸት ይገባል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ሴቶችንና ወጣቶችን በማደራጀት በዘርፉ የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ዶክተር ግርማ ሞገስ እና ከአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በኩል ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
አዲሱ የስንዴ መውቂያ ማሽን በሀገር ውስጥ ገበያ በማንኛውም አካባቢ በሚገኝ ጥሬ እቃ መመረት እንደሚቻልም ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በ2015 ገበያ ዋጋ የማሽኑ ማምረቻ 143 ሺህ 9 መቶ 27 ብር ሲሆን ይህም ከውጭ ከሚመጣው ከ25-35 በመቶ ቅናሽ ያለው መሆኑ ተገልጿል።
ማሽኑ ገለባውን አርሶ አደሩ በሚፈልገው መጠን የሚያደቅ ሲሆን አርሶ አደሩ "Walking tractor" ተጠቅሞ መውቃት ይችላልም ተብሏል።
አዲሱ የስንዴ መውቂያ ቴክኖሎጂ በሰዓት ከ13 እስከ 18 ኩንታል የሚመዝን የስንዴ ነዶ መውቃት እንደሚያችልም ተገልጿል።