ቀጥታ፡

"የህግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ በኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

አርባ ምንጭ፤ ሰኔ 19/2015(ኢዜአ)፡- "የህግ የበላይነትና የመልካም አስተዳደር ግንባታ በኢትዮጵያ" በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለና የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ተገኝተዋል።

በተጨማሪም የተለያዩ የፌዴራልና የክልሎች የፍትህ አካላትና ሌሎች እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።


 

በፍትህ ሚኒስቴር አዘጋጅነት ለሁለት ቀናት የሚቆየው የምክክር መድረኩ ዓላማ በህግ የበላይነት፣ በመልካም አስተዳደርና በፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ እንዲሁም በህግ የበላይነት ግንባታ የአስተዳደር ተቋማትና ባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ግንዛቤ ለማሳደግ መሆኑ ተመልክቷል።

በመድረኩ በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የፍርድ ቤቶችና የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም